የኢትዮጵያ ሠላም ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና መረጋጋት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው – ደቡብ ሱዳን
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አምባሳደር ነቢል ማኅዲ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንታዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ባርናባ ማሪያል ቤንጃሚን ቢል ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
አምባሳደር ነቢል፥ የኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ ሠራዊቱ ወደ ትግራይ ክልል ዘልቆ እንዳይገባ ማዘዙ እና የፖለቲካ ሰዎችን ከእስር ቤት መፍታቱ በኢትዮጵያ ሠላም ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ሁሉን አቀፍ ውይይት ለመጀመር ማቀዱንም ለሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አምባሳደር ነቢል ፥ የኢትዮጵያ መንግስት 35ኛውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ እና 40ኛውን የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት መደበኛ ሥብሰባ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ያደረገውን ዝግጅትም አብራርተዋል።
ሚኒስትሩ በበኩላቸው፥ ሠላም የሰፈነባትና የተረጋጋች ኢትዮጵያን በማየታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መረጋጋትም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሠላም ለማስፈን ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመው፥ በእኛ በኩል የኢትዮጵያን መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ምንም አይነት ነገር የለም ሲሉም ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።