የተለያዩ ተቋማት ለሰራዊቱና ለአፋር ክልል ተፈናቃዮች ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሕብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለመከላከያ ሰራዊትና ለአፋር ክልል ተፈናቃዮች ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕብረተሠብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአገር መከላከያ ሰራዊት 5 ሚሊየን 200 ሺህ ብር በላይ የሚገመት አልባሳት ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፥ የተደረገው ድጋፍ 5 ሚሊየን 200 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ አንሶላዎች፣ ቢጃማና ነጠላ ጫማዎች ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሊዊጂ በበኩላቸው፥ የጤናው ዘርፍ በዚህ ፈታኝ ወቅት ለሀገር እያደረገ ያለው አበርክቶ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢንስቲትዩቱ ያደረገው ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊት የሚሰጠው አገልግሎት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ሲሚንቶ አከፋፋዮች ማህበር በጋራ በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ዜጎች የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ድጋፉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስረክበዋል፡፡