በደቡብ ኦሞ ዞን 77 ሺህ ዜጎች ለድርቅ ተጋላጭ መሆናቸው ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ጥር 26፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች የምግብ ድጋፍ መደረጉን የፌደራል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ከፋና ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የደቡብ ክልል ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የምግብ ድጋፋን የማድረስ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዞኑ በድርቁ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ 11 ሺህ ኩንታል ምግብ ተዘጋጅቶ ወደ ዞኑ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ድጋፋ በመንግሥት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመ፥ ህፃናት፣ እናቶችንና አቅመ ደካሞችንም ታሳቢ ያደረገ የአልሚ ምግቦችም መላኩን ተናግረዋል።
በቅርቡ ጥያቄ ያቀረበው ምስራቅ ባሌ 251 ሺህ ሰዎች በድርቁ ምክንያት ለእርዳታ መዳረጋቸውን ተከትሎም ኮሚሽኑ 42 ሺህ ኩንታል የምግብ እርዳታ በመጓጓዝ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
በጉጂ ዞንም 46 ሺህ 790 ሰዎች በድርቅ መጠቃታቸውን ተከትሎ ከ7 ሺህ ኩንታል በላይ ምግብ ተልኳል ብለዋል።
በቦረና ዞን ቀድሞ ሲረዱ ከነበሩት ጋር ተደምሮ በዞኑ ከ426 ሺህ በላይ ተጎጂዎች በመኖራቸው መንግስት ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛልም ነው ያሉት።
በሶማሌ ክልል ቀድሞ ከነበሩ የተረጂዎች ቁጥር ጋር ተዳምሮ በአሁኑ ሰዓት የተጎጂዎች ቁጥር 3 ሚሊየን 360 ሺህ መድረሱን ገልጸው፥ የድጋፍ ስራውም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
የድርቁ ሁኔታ በቀጣይ ሁለት ወር እንደሚኖር ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፥ የከብቶች መኖን የማልማትና የመረዳዳቱ ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በብርሃኑ በጋሻው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!