የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የአየር አገልግሎት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያደረገቻቸውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ አመት 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው፡፡
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማሕዲ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳቦች ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
በሪፖርታቸውም የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆቹ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የአየር ትራንስፖርት መዳረሻዎችን በማስፋት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያላቸው ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ከአየር አገልግሎት ስምምነቶቹ መካከል በኢትዮጵያ መንግሥትና እና በሴራሊዮን ሪፐብሊክ መንግሥት በኩል የተፈረመው አንዱ ነው፡፡
ስምምነቱ ለአየር መንገዶች ወደ ተመረጡ መዳረሻዎች በቀጥታ ለማረፍና ምቹ የአቪዬሽን አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑ አንስተዋል።
ምክር ቤቱ የአየር አገልግሎት ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1417 /2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡
በመቀጠል በአንጎላ ሪፐብሊክ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተፈረመው የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን÷ ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ ግንኙነት ለማሳደግ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ም/ሰብሳቢዋ አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ ምክር ቤቱ ይህን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1418 /2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በባንግላዴሽ ሕዝባዊ ሪፐብሊክ መካከል የተደረገው የአየር አገልግሎት ስምምነት በሀገራቱ መካከል እያደገ የመጣውን የአየር ትራንስፖርት ፍሰት ከግምት ያስገባ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በተመሳሳይ ምክር ቤቱ ይህን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1419/ 2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ሌላው በምክር ቤቱ የጸደቀው የአየር አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኢስዋቲኒ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት መካከል የተደረገው ስምምነት ነው፡፡
ስምምነቱ ያለ በረራ ድግምግሞሽ ገደብ የጭነት በረራዎችን ማከናወን ጨምሮ ለበረራ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ማስገባትን የሚያካትት በመሆኑ የበረራ ወጪን እንደሚቀንስ ገልፀዋል፡፡
ምክር ቤቱ ይህንንም ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1420/ 2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በሳራ ስዩም