ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የአረንጓዴ ልማት መደገፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፍ አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩትና የዓለም ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ እያደረገች ያለውን ጥረት መደገፍ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
የመግባቢያ ስምምነቱን የዓለም አቀፍ አረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ፍራንክ ሪጅስቤርማን እና የዓለም ሪሶርስ ኢንስቲትዩት የውል ጉዳይ ተወካይ ጄፍ ሊን ናቸው የተፈራረሙት።
ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ላይ እያደረገች ያለችውን ጥረት ለመደገፍ የሚያስችል የትብብር ማዕቀፎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
በተለይም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ምርምር፣ የአየር ንብረት መርሀ ግብር፣ ፍላጐትን ያማከለ ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ለመስጠትም ያስችላል ነው የተባለው።
ተቋማቱ በመግባቢያ ስምምነቱ የተካተቱ ግቦችን ለማሳካት የኢትዮጵያን የ10 ዓመታት ስትራቴጂያዊ የልማት እቅድ ትግበራ ለመደገፍ ይተባበራሉም ተብሏል።
ኢትዮጵያ በረጅም ጊዜ የአየር ብክለትን ለመቀነስ አቅዳ እየሰራች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ፥ ይህ እቅድ እውን እንዲሆን ሁለቱ ተቋማት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ኢዜአ ዘግቧል።
በካርቦን ልቀት ቅነሳ፣ በሀብት አጠቃቀምና ሌሎች ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ ከእቅድ እስከ ትግበራ በትብብር እንደሚሰሩም ተመላክቷል።