ባለፉት 6 ወራት ከ26 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የህክምና ግብዓቶች አስፈላጊው ቁጥጥር ተደርጎባቸው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ከ26 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች አስፈላጊው ቁጥጥር ተደርጎባቸው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ነው የመድኃኒቶች ደህንነት፣ ጥራት፣ ፈዋሽነት እና አግባባዊ አጠቃቀም ቁጥጥርን ለማሻሻል በተሰራው ስራ ከ26 ቢሊየን ብር በላይ መድኃኒትና የህክምና መሣሪያ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ያደረገው ፡፡
በሌላ በኩል ግምታቸው ከ32 ሚሊየን ብር በላይ የሆኑ የመድኃኒት፣ የሕክምና መሣሪያ ምርቶችና የመድኃኒት ግብዓቶች የጥራት፣ የደህንነት፣ የፈዋሽነት እና ውጤታማነት መስፈርት ሳያሟሉ ሳይመዘገቡ ወደ ሀገር ውስጥ በህገወጥ መንገድ ሲገቡ በመቆጣጠር እንዳይገባ በማድረግ፤ በህብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ በሀገር ውስጥ በሚገኙ የመድኃኒት ተቋማት በተከናወነ ቁጥጥር፥ የተለያዩ 44 የሚሆኑ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ የሚያመርቱ ድርጅቶችና ጅምላ አከፋፋይ ተቋማት የተበላሹና አገልግሎት ላይ የማይውሉ፣ ያልተመዘገቡ መድኃኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪዎች ይዞ መገኘት እና በተለያዩ ጉድለቶች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ የዕገዳ እንዲሁም የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት የመሰረዝ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!