በኢትዮ- ሱዳን የሚታዩ የውስጥ ውጥረቶች እንዲረግቡ በማድረግ የነበረንን ወዳጅነት አጠናክረን መቀጠል አለብን – የሱዳን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያና ሱዳን የሚታዩ የውስጥ ውጥረቶች እንዲረግቡ በማድረግ የነበረንን ወዳጅነት አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ የሱዳን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ኢማድ ዲን ኢብራሄም አል ሃጃዚ አስታወቁ፡፡
በደቡብ አፍሪካ የኢፈዴሪ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ከደቡብ አፍሪካ የሱዳን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ኢማድ ዲን ኢብራሄም አል ሃጃዚ ጋር በኢትዮጵያና ሱዳን የሁለትዮሽ እና በክፍለ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በደቡብ አፍሪካ የኢፈዴሪ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አቶ ሙሉጌታ ውለታው በውይይቱ ወቅት እንዳሉት፥ የሁለቱ አገራት መንግስታትና ህዝቦች ግንኙነት ጠንካራና ታሪካዊ በመሆኑ ይህንኑ ማስቀጠል ሁሌም የኢትዮጵያ ፍላጎት ነው።
በቅርቡ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸው፣ የመተማ- ገላባት ድንበር መከፈት፣ የተቋረጠው የሁለቱ አጎራባች ክልሎች የጋራ ስብሰባ እንዲጀመር ማድረጋቸው እና የድንበር ህዝቦች የንግድ ልውውጥ መጀመራቸው የሁለቱ እህትማማች ህዝቦችን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር በጎ እርምጃ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ እና የህዝቦችን አንድነት ለማጎልበት መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን ያብራሩት ምክትል ሚሲዮን መሪው ፥ በአሁኑ ወቅትም አገራዊ የምክክር መድረክ የሚያመቻች ኮሚሽን በማቋቋም ወደ ሥራ እየተገባ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብም የመጀመሪያ ዙር ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ለሁለቱ አገራት ትልቅ ብሥራት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ ፥ ይህም የሁለቱን አገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት እንደሚያጎለብት አስታውቀዋል።
የክፍለ አህጉራዊ ድርጅቱን በተለይም ኢጋድን በጋራ በማጠናከር መረጃንና ልምዶችን የመለዋወጥ እንዲሁም በጋራ ጉዳዮች ላይ የሚኖረው መደጋገፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያላቸውን ፍላጎት አስረድተዋል።
የሱዳን ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ኢማድ ዲን ኢብራሄም አል ሃጃዚ በበኩላቸው ፥ በሁለቱም አገራት የሚታዩ የውስጥ ውጥረቶች እንዲረግቡ በማድረግ የነበረንን ወዳጅነት አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።
ጠንካራ ኢትዮጵያ መኖሯ ለጠንካራ ሱዳን መኖር ወሳኝ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት ሱዳን ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስረድተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተም በ2015ቱ የመሪዎች ስምምነት መሠረት ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ እና በግድቡ ኦፕሬሽን ላይ መረጃ መለዋወጥ አስፈላጊ መሆኑን የሱዳን መንግስት እንደሚያምን ጠቅሰው ፥ በቅርቡም ውይይቱ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳለ መግለጻቸውን በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!