በአዲስ አበባ በአንድ ኮንዶሚኒየም ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የአንድ ህፃን ህይወት ሲያልፍ በሁለት ልጆች ላይ ጉዳት ደረሰ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በአንድ ኮንዶሚኒየም ህንፃ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ የአንድ ህፃን ህይወት ሲያልፍ በሁለት ልጆች ላይ ደግሞ ጉዳት ደረሰ።
አደጋው በክፍለ ከተማው ወረዳ 4 አራብሳ ኮንዶሚኒየም ብሎክ 34 ሁሌተኛ ፎቅ ላይ በሚገኝ የመኖሪያ ቤት ላይ ነው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ከሃያ አካባቢ የደረሰው።
በእሳት አደጋው የስድስት ዓመት ህፅን ልጅ ህይወቱን ሲያጣ የአስር ዓመት ዕድሜ ያላት የሟቹ እህት ደግም በጭስ የመታፈን አደጋ ደርሶባታል።
እሳቱ በተፈጠረ ወቅት በቤት ውስጥ የነበረችው የ18 ዓመት ወጣት የቤት ሰራተኛም ከሁለተኛ ፎቅ ዘላ በመውረድ ራሷን ለማዳን ባደረገችው ሙከራ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባታል።
ተጎጂዎቹ የህክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን በአዲስ አበባ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
በእሳት አደጋው 50 ሺህ ብር የተገመተ ንብረት የወደመ ሲሆን፥ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ባደረጉት ርብርብ እሳቱ ተዛምቶ ከዚህ የከፋ ጉዳተ ሳያደርስ መቆጣጠር ተችሏል ነው ያሉት።
የደጋው ምክንያትኝ ከኤሌክትሪክ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ነው አቶ ንጋቱ የነገሩ።
በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ አልፎ አልፎ መሰል የእሳት አደጋ እያጋጠመ ነው ያሉት አቶ ንጋቱ፥ የትናንቱን ጨምሮ አብዛኛው የአደጋ መንስኤ ደግሞ ከኤሌክትሪክ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ አመልክተዋል።
በመሆኑም የኤሌክትሪክ አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ነው አቶ ንጋቱ የመከሩት።
የጥንቃቄው አካል ሆኖም የመኖሪያ ቤቶችን የኤሌክትሪክ መስመር በየጊዜው በባለሙያ ማስፈተሽም እንዲሁ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።
ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ደግሞ የህንፃዎች የአደጋ ጊዜ መውጫ መሆኑን አንስተዋል። በኮንዶሚኒየምና በመኖሪያ አፓርትመንቶች እንዲሁም ደግሞ በአገለግሎት መስጫዎች ህንፃዎች ላይ የአደጋ ጊዜ መውጫ ደረጃዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።
ትናንት ከአደጋው ራሷን ለማትረፍ ብላ ከአምስተኛ ፎቅ በመዝለል ከባድ ጉዳት የደረሰባት ወጣት ለአደጋ ጊዜ መውጫ አስፈላጊነት እንደ አንድ ማሳያ ሊነሳ እንደሚችል በመጥቀስ።
አደጋን ከመቀነስ አኳያም ከህንፃዎች የውጪኛው ክፍሎች ላይ የአደጋ ጊዜ መውጫዎችን መግጠመ የሚቻልባቸው አማራጮች ካሉ መመልከት ይገባል ብለዋል።
ከዚህ ባሻገርም በአንዳንድ የጋራ የመኖሪያ ቤት ህንፃዎች ላይ ለአደጋ አጋላጭ የሆኑ ያልተጠናቀቁ ግንባታዎች እንደሚታዩ በመግለፅ፥ ለአብነትም የህንፃ መወጣጫ አሳንሰር ወይም ሊፍትን ጠቅሰዋል።