ከተማ አስተዳደሩ በአፋርና በቤኒሻንጉል ክልሎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ57 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአፋርና በቤኒሻንጉል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚሆን ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ፡፡
ድጋፉ ከህብረተሰቡና ከተለያዩ ባለሀብቶች የተሰበሰበ ሲሆን÷ በአፋር ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚሆን ነው ተብሏል፡፡
ከ57 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የእለት ደራሽ ምግብ እና አልባሳት የተካከቱበትን ድጋፍ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለሁለቱም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች አስረክበዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በርክክቡ ወቅት÷ በሌሎች ላይ የደረሰው ችግር በዚያ አካባቢ እንደደረሰ ችግር ብቻ የምናየው አይደለም ያሉ ሲሆን÷ የራሳችን የእኛው ችግር በመሆኑ መደገፍና አብሮ መቆም ግዴታችን ነው ብለዋል፡፡
የተጀመረው ድጋፍ በሁሉም መስክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው÷ በአፋር ክልል 6 ጤና ጣቢያዎችን መልሶ ለማደራጀት እንዲሁም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች የአፋር ማዘጋጃ ቤቶችን መልሶ ለማደራጀት ሃላፊነት ወስደው ሰፊ ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው÷ አዲስ አበባ የአፋር ህዝብ አምባሳደር ነው ሲሉ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባም የሁላችንም እናት ናት ይህንንም በተደጋጋሚ በተግባር አሳይታለች ብለዋል፡፡
በተለይ የኑሮ ውድነት ፈተና በሆነበት ወቅት የከተማው ህዝብ ከወገኖቹ ጎን ለመቆም እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ትልቅ ክብር ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ከለውጡ በኋላ ለሁሉም ህዝብ እያደረገ ያለው ድጋፍ እጅግ ከፍተኛ ነው ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ናቸው፡፡
በከተማ አስተዳደሩ እየተደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ ነው ማለታቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!