Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹ ቁጥር ከ60 ሚሊየን አለፈ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞቹ ቁጥር ከ60 ሚሊየን ማለፉን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ አስታወቁ፡፡

የኢትዮ- ቴሌኮም የግማሽ ዓመት አፈፃፀም በገንዘብ ሚኒስቴርና በመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በተገመገመበት ወቅት የድርጅቱ አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 60 ነጥብ 8 ሚሊየን መድረሱ  ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንደገለጹት÷  በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ድርጅቱ 28 ቢሊየን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡

74 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱንና ከስምንት ወራት በፊት ሥራ ላይ ባዋለው የቴሌ ብር አገልግሎት 13 ነጥብ 1 ሚሊየን ደንበኞችን በማፍራት 16 ነጥብ 6 ሚሊየን ክፍያዎች በመተግበሪያው አማካይነት መንና በገንዘብ  የ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ልውውጦች መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

የወጪ ቅነሳ የአሰራር ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ወጪ ማስቀረት ችያለሁ ያለው ድርጅቱ÷ 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለዕዳ ክፍያ ማዋሉን፣ እንዲሁም 12 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የታክስ ክፍያ መፈፀሙን ገልጿል፡፡

ድርጅቱ ከግማሽ ዓመቱ ዕቅድ 86 በመቶውን እንዳሳካ የተገለጸ ሲሆን÷ የፀጥታ ችግር፣ የመሰረተ ልማትና ንብረት ጉዳት፣ በክልሎች አግባብ ያልሆነ ካሳ ጥያቃና የባንክ ሂሳብ መዘጋት ለሥራው ዋና ዕንቅፋት እንደነበሩ ተመልክቷል፡፡

የግምገማ መድረኩን የመሩት የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው፥ ኢትዮ ቴሌኮም ባለፋት 6 ወራት አገልግሎቱን በማስፋፋት፣ የአግልግሎቱን ጥራት በማሻሻል፣ የገጠሙትን ፈተናዎች ለማለፍ፣ በተለይም የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ጠንክራ ሥራ መስራቱን ገልጸዋል።

ኩባንያው ይበልጥ ትርፋማ እንዳይሆን ምክንያት የነበሩ ደንቦችና አሰራሮችን መንግስት ለማሻሻል መስራቱን ተናግረው÷ ወደፊትም ለሚገጥሙት ችግሮች በጋራ መፍትሔ ለመስጠት ይሰራል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ኩባንያው ራሱን ለውድድር በበቂ ሁኔታ ማዘጋጀት እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.