የዓድዋ ድል የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ዋልታ፣ የመተባበራችን ውጤት ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ዋልታ፣ የመተባበራችን ውጤት ነው አለ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
ነገ የሚከበረውን 126ኛው የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም “ዛሬ ላይ ያለ ትዉልድ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሉዓላዊነታችንና የነፃነታችን መከታና ጋሻ መሆኑን በመገንዘብ የጥንካሬአችን ምንጭ የሆነዉን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን መጠበቅ ይኖርበታል” ብሏል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የአድዋ ድል የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ዋልታ፣ የመተባበራችን ዉጤት ነዉ
የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን በአንድ ታሪካዊ የጦር ሜዳ ተዋግተዉ ጠላትን ድል የማድረግ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም የአድዋ ድል የጠንካራ ሉዓላዊና ኅብረ ብሔራዊት አገር ግንባታ ሂደት ይበልጥ የተረጋገጠበት፣ የአገራዊ ኩራታችን ምንጭ ነዉ፡፡
በርግጥ በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያዊያን የገጠሙትን ጦር፣ እንኳንስ ተዋግቶ ድል ማድረግ ይቅርና፣ ለመዋጋት ማሰብ በራሱ አዳጋች ነበር፡፡ በወቅቱ ወራሪዉ የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በኃይል አንበርክኮ ቅኝ ለመግዛት የሚያስችለዉ በቂ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ታጥቋል፡፡ በሌላ በኩል በበቂ ሁኔታ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ያልነበራት ኢትዮጵያ፣ ወራሪዉን ኃይል ገጥማ ታሸንፋለች ብሎ ማሰብ ፈፅሞ አይቻልም ነበር፡፡ ሆኖም ግን በታጠቁት የጦር መሳሪያና በነበራቸዉ ወታደራዊ አደረጃጀት ሳይሆን በሰነቁት ወኔ እና የአልገዛም ባይነት ሥነ ልቦና እስከ አፍንጫዉ ታጥቆ የመጣዉን የወራሪዉን ኃይል ድል በማድረግ ዉርደት አከናንበዉ እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ ድሉ በዓለማችን ያልተለመደና ያልተገመተ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ ተመዘገቧል፡፡
በአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ ማሸነፍ ለበርካቶች ምሥጢር ቢሆንም ለኢትዮጵያዊያን ግልፅ ነበር፤ የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ምሥጢሩ አንድነታችን፣ ነፃነት ወዳድነታችንና የአልገዛም ባይነታችን አገራዊ እሴቶች ነበሩ። ኢትዮጵያ በባእዳን ጠላት ስትወረር ለአገር ክብርና ሉዓላዊነት ለመፋለም የተሰለፉት ኢትዮጵያዊያን ከአንድ ብሔር የመጡ አልነበሩም። በባህልና በቋንቋ ወይም በሃይማኖት ኅብር ነበሩ። በትዉልድ አካባቢ አይተዋወቁም፡፡ የጋራ ዓላማ ግን ነበራቸው። እርሱም በነጻነት መኖር ነው። የሚጋሩት ቋንቋና ብሔርን ሳይሆን አገር ወዳድነትንና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣዉን ጀግንነት ነበር፡፡ የአንድነታቸው ምንጭ በአንድ ቋንቋ መናገር፣ በአንድ አካባቢ መኖር አልነበረም። ለአንዲት ሀገር ሉዓላዊነት ለመሞት የነበራቸው ቆራጥነት እንጂ። የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በጋራ ተዋግተዉ ጠላትን ያሸነፉበት ጦርነት ብቻም ሳይሆን አባቶቻችን በደማቸዉና በአጥንታቸዉ ያኖሩልን የጋራ ቃል ኪዳን ነዉ፡፡
የአድዋ ድል የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ድል ከመሆኑም በላይ ጊዜ የማይሽረዉ በደምና በአጥንት የተፃፈ የጋራ ታሪካችን ጭምር ነዉ፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከት የአድዋ ድል ትሩፋት ከጦር ሜዳ አሸናፊነት በላይ ነዉ፡፡ አገራዊ እንድነታችንና ሉዓላዊነታችን የተረጋገጠበት ታሪካዊ ድል ነው፤ አድዋ፡፡ የአሸናፊነታችን ምሥጢር መተባበራችንና አንድነታችን ስለመሆኑ አባቶቻችን በተግባር ያስተማሩበት የተግባር ልምምድም ነበር፡፡ መላዉ ኢትዮጵያዊያን ያለ አንዳች ልዩነት በአንድነት ለአገራቸዉ ሉዓላዊነትና ለሕዝቦቿ ክብር ተሰልፈዉ በጋራ የተዋደቁና የጋራ ድል ያስመዘበገቡ በመሆናቸዉ የአድዋ ድል የጋራ ታሪካችን ነዉ፡፡ ከሁሉም በላይ አድዋ የብሔራዊ ኩራታችን ምንጭም ነዉ፡፡ ከኢትዮጵያም አልፎ የመላ ጥቁር ሕዝቦች ኩራት ነዉ፡፡ የአድዋ ድል የአፍሪካዊያን የነፃነት ፋና ወጊ በመሆን የነፃነት ትግል ማቀጣጠያ ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም ተምሳሌት ተደርጋ አንድትቆጠር አድርጓታል፡፡
በአድዋ ጦርነት የተመዘገበዉ ድል በጠላት ድክመት ሳይሆን በአንድነታችን ጥንካሬ ነዉ፡፡ ጠላት ዛሬም ሆነ ነገ መኖሩ አይቀርም፡፡ የጠላታችን ምኞት የሚከሽፈዉ ግን በጠላታችን መዘናጋት ሳይሆን በዉስጣዊ አንድነታችን ጥንካሬ ነዉ፡፡ በታሪካችን ጠላት ሲያጠቃን ብቻዉን ቆሞ፣ ራሱን ችሎ አይደለም፡፡ ከዉስጣችን በሚፈልቁ ባንዳዎችና ተላላኪዎች በመታገዝ ጭምር ነዉ፡፡ ልክ እንደ አድዋ ድል ሁሉ የዛሬም ሆነ የነገ ጠላታችንን ማሸነፍ የምንችለዉ ዉስጣዊ ጥንካሬአችንን በማጉላት፣ ከዉስጣችን ከሚፈልቁ ባንዶች በመጠንቀቅ መሆን አለበት፡፡ የዘንድሮዉን 126ኛዉ የአድዋ ድል በዓልን ስናከብር አድዋ የጦር ሜዳ አሸናፊነት መታሰቢያ እለት ብቻ ሳይሆን የአድዋ ትሩፋቶችን በመጠበቅ፣ የአሸናፊነታችን ምሥጢር ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መሆኑን በአግባቡ በመረዳት መሆን አለበት፡፡
ዛሬ ላይ ያለ ትዉልድ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሉዓላዊነታችንና የነፃነታችን መከታና ጋሻ መሆኑን በመገንዘብ የጥንካሬአችን ምንጭ የሆነዉን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ዛሬ ያለን ወጣቶች፣ ምሁራንና ፖለቲከኞች የአድዋ ድል የጋራ ታሪካችን፣ የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ዋልታ፣ የጥንካሬአችን ምንጭ መሆኑን በመገንዘብ ታሪኩ በደማቅ ገድል ታጅቦ ለቀጣይ ትዉልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል፡፡
ዛሬ ላይ ያለ ትዉልድ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሉዓላዊነታችንና የነፃነታችን መከታና ጋሻ መሆኑን በመገንዘብ የጥንካሬአችን ምንጭ የሆነዉን ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ዛሬ ያለን ወጣቶች፣ ምሁራንና ፖለቲከኞች የአድዋ ድል የጋራ ታሪካችን፣ የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ዋልታ፣ የጥንካሬአችን ምንጭ መሆኑን በመገንዘብ ታሪኩ በደማቅ ገድል ታጅቦ ለቀጣይ ትዉልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት