በክልሎቹ በጦርነቱ ሳቢያ የደረሰውን የምርት ክፍተት ሊያካክስ የሚችል የበጋ መስኖ ልማት እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣የካቲት 22፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ እና ደቡብ ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት በመኸር ላይ የደረሰውን የምርት ክፍተት ሊያካክስ የሚችል የበጋ መስኖ ልማት እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ በክልሉ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት 38 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡
በአማራ ክልል በበጋ መስኖ የሚለማውን መሬት 80 ሺህ ሄክታር በስንዴ ለመሸፈን እየተሰራ ነው ያሉት ምክትል ሃላፊው፥ 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
በደቡብ ክልል በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በበኩላቸው÷ በክልሉ በመጀመሪያ ዙር የበጋ መስኖ ልማት ከ20 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በደቡብ ክልል ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል የተሸፈነ ሲሆን፥ በዚህም ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
በሁለቱም ክልሎች በበጋ መስኖ እየለሙ የሚገኙ የተለያዩ ሰብሎች በተለያየ እና በጥሩ ቁመና እንደሚገኙም ሃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን