Fana: At a Speed of Life!

የውንብድና ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ተከሳሾች ጌታነህ አቸነፍ እነ ሞገስ ሙሉጌታ ከሌላ ካልተያዘ ግብረ አበራቸው ጋር በመሆን በፈፀሙት የውንብድና ወንጀል በዓቃቢ ህግ ክስ ተመስርቶባቸው በ5 ዓመት ከ4 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ተወሰነባቸው፡፡

ግለሰቦቹ በእስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ እና 670 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ መሆኑ ተመልክቷል።

የክስ መዝገቡ እንደሚስረዳው፥ ተከሳሾች ከሌላ ካልተያዘ ግብረ አበራቸው ጋር በመሆን የማይገባቸውን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ታህሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 11 ከ 30 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታው ቦሌ ለሚ ኢንዳስትሪ ፓርክ አካባቢ የግል ተበዳይ ሰናይት አድምቀው የተባለቸውን ግለሰብ 2ኛው ተከሳሽ አንገቷን አንቆ ሲይዛት 1ኛ ተከሳሽ ደግሞ ግምቱ 14 ሺህ ብር የሚያወጣ አይፎን ስልክ ከእጇ ላይ ነጥቆ የወሰደባት በመሆኑ ክስ ቀርቦባቸዋል።

እንዲሁም በሁለተኛ ክስ ሁለቱም ተከሳሾች ካልተያዘ ግብረ አበራቸው ጋር በመሆን ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለማግኘት በማሰብ በ1ኛ ክስ ላይ በተጠቀሰው ቀን ሰዓት እና ቦታ የግል ተበዳይ መስፍን ደመላሽን 1ኛ ተከሳሽ ከኋላ በኩል አንገቱን አንቆ ሲይዘው ያልተያዘው አባሪ ደግሞ በሁለት እጁ የተበዳይን እጁን እንዳይከላከል አጥብቆ በመያዝ እና የተበዳይን ቀበቶ ፈትቶ ሁለት እግሮቹን ሲያስረው 2ኛ ተከሳሽ ቴክኖ ተንቀሳቃሽ ስልክ የዋጋ ግምቱ 4 ሺህ ብር እና ጥሬ ገንዘብ 375 ብር በአጠቃላይ 4 ሺህ 375 የወሰዱበት እና መሬት ላይ የጣሉት በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የውንብድና ወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡

ተከሳሾች በችሎት ቀርበው የዕምነት ክደት ቃላቸውን ሲጠየቁ ድርጊቱን አልፈፀምን በማለት ክደው የተከራከሩ በመሆኑ ዓቃቢ ህግ ክሴን ያጠናክሩልኛል ያላቸውን የሰው፣ የሰነድ እና የኤግዚቢት ማስረጃዎችን በማቅረብ አስረድቷል፡፡

ችሎቱም ይህንን ካየ እና ከመረመረ በኋላ ተከሳሾች እንዲያስተባብሉ ቢጠይቅም ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል፡፡

በዚህም መሰረት ፍ/ቤቱ መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሾችን ያርማል መሰል አጥፊዎችንም ያስተምራል በማለት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ5 ዓመት ከ4 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማስተላለፉን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.