ምዕራብ ዕዝ ከሕግ ማስከበር እስከ ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከፍተኛ ድል ያስመዘገበ ነው – ጀኔራል አበባው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምዕራብ ዕዝ ከሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው እስከ ዘመቻ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከፍተኛ ድል ያስመዘገበ መሆኑን የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ተናገሩ፡፡
በምዕራብ ዕዝ ለሠራዊቱ አመራሮች የወታደራዊ ሳይንስ እና የአመራር ጥበብ ስልጠና ተሰጥቷል።
ጀኔራል አበባው ታደሰ ስልጠናውን ለወሰዱ አመራሮች በሰጡት መመሪያ÷የምዕራብ ዕዝ የሠራዊት አባላት እና አመራሮች ከሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው ጀምሮ እስከ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በድል በመወጣት ሀገርን ከብተና ህዝብን ከእልቂት እና ስቃይ መታደግ ችለዋል ነው ያሉት።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገራችንን ለማሸበር የከፈተብንን ጦርነት መቀልበስ የተቻለው ከአመራር እስከ ታችኛው የሠራዊት አባል ባለው የሀገር ፍቅር ስሜት እና ቁርጠኝነት ነው ብለዋል።
አመራር ሁለገብ ብቃት እና ልምድ ሲኖረው የሚመራውን ክፍል በስልጠና ያዘጋጃል ያሉት ጀነራል አበባው÷ሠራዊት ሰልጥኖ ለግዳጅ ዝግጁ ሆኖ ሲጠብቅ ውጊያን በአጭር ጊዜ እና ባነስተኛ ኪሳራ ድልን ማስመዝገብ እንደሚቻል አስረድተዋል።
የዕዙ አመራሮች በስልጠና ያገኛችሁትን ወታደራዊ የአመራር ጥበብ ወደ ተግባር በመለወጥ ቀጣይ ለሚሰጣችሁ ግዳጅ ራሳችሁን እና ሠራዊቱን ማዘጋጀት ይኖርባችኋል ሲሉ ማሳሰባቸውንም ከመከላከያ ሠራዊት ፌስቡክ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሰለ መሠረት ስልጠናውን ለወሰዱ አመራሮች የምስክር ወረቀት አበርክተዋል፡፡