Fana: At a Speed of Life!

ከባሕር ዳር- ዳንግላ በሚሄደው 66 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ አስተላለፊ መስመር ስርቆት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባሕር ዳር- ዳንግላ በሚሄደው 66 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ አስተላለፊ መስመር ላይ የታወር ብረት ስርቆት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች እየተያዙ መሆኑን የባሕርዳር ከተማ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
 
የከተማ አስተዳደሩ 8ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ የቴክኒክ ምርመራ ተወካይ ሳጅን ስጦታው ንጉሤ÷ አስካሁን ወንጀሉን በመፈጸም የሰባት ተጠርጣሪዎች ጥቆማ የደረሳቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
ከእነዚህ ውስጥም ሁለት ተጠርጣሪዎች በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር አዲስ ዓለም ቀበሌ በአካባቢው አስተዳደርና የፀጥታ አካላት ቅንጅት መያዛቸውን ጠቁመው÷ ቀሪ ያልተያዙ ተርጣሪዎችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
 
ከታወር ላይ ብረትን በመፍታትና በመጋዝ በመቁረጥ በተፈፀመው ስርቆት ምክንያት ካባሕር ዳር -ዳንግላ የሚሄደው ኤሌክትሪክ አስተላለፊ መስመር በመውደቁ ከዳንግላ እና ፓዌ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኤሌክትሪክ የሚያገኙ ዳንግላ፣ ዱርቤቴ፣መራዊ፣ ኮሶበር፣ ግምጃ ቤት፣ ቻግኒ፣ ግሽ ዓባይ፣ ቅላጅ እና በአካባቢያቸው ያሉ ከተሞች መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም ቀን 9፡00 እስከ መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ምሽት 12፡00 ሰዓት ድረስ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸው መቀየቱ ይታወሳል፡፡
 
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠርጣሪዎችን ለያዙና ቀሪዎችን ለመያዝ ጥረት እያደረጉ ላሉ የአስተዳደር እና የፀጥታ አካላት ምስጋና አቅርቧል፡፡
 
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት በአገልግሎት ተደራሽነትና ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ሲሆን÷ ደንበኞች ላይም ኪሳራና እንግልት እያስከተለ መሆኑን ከአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.