በደቡብ ክልል የወባና ያልተመጣጠነ የምግብ እቅርቦት ችግሮች መከሰታቸውን ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 16 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የወባና ያልተመጣጠነ የምግብ እቅርቦት ችግሮች በክልሉ መከሰታቸውን የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ አስታወቁ፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ከፋና ብሮድካስቲንግ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፥ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ትግበራ ወጥነት ባለው መልኩ እንዲከናወን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የወባና የምግብ አለመመጣጠን ችግሮች በክልሉ መከሰቱን መረጃዎች ያሳያሉ ያሉት ሀላፊው ፥ እነዚህ የጤና ችግሮች እንዳይቀጥሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከጤና አገልግሎት ጋር በተያያዘ በቅድመ ወሊድና ድህረ ወሊድ አገልግሎት እንዲሁም የኤች አይ ቪ ምርመራና የቲቪ በሽታ ልየታን አስመልክቶ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ዜጎች በተሻለ ደረጃ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
የእናቶች ሞትን በተመለከተ በየዓመቱ ለውጥ ያለው ቢሆንም ባለፋት ስድስት ወራቶች የ160 እናቶች ሞት የተከሰተ በመሆኑ ህይወት እየሰጡ ህይወታቸውን እንዳያጡ ልንታደጋቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በሰለጠኑ ባለሞያዎች የሚሰጥ የወሊድ አገልግሎት አምና 74 በመቶ ከነበረበት አሁን ላይ ወደ 80 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል፡፡
የቢሮው ሀላፊ አክለውም ፥ መንግስት ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በብርሃኑ በጋሻው ፣ በማቲዎስ ፈለቀና ጥላሁን ይልማ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!