የፋና ላምሮት የባለተሰጥዖ ድምፃውያን ውድድር ነገ ፍፃሜውን ያገኛል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምዕራፍ ዘጠኝ የ”ፋና ላምሮት” የባለተሰጥዖ ድምፃውያን ውድድር ነገ ፍፃሜውን ያገኛል።
እንደሚታወቀው ላለፉት ስምንት ሣምንታት ሲካሄድ የቆየው የ“ፋና ላምሮት” የምዕራፍ 9 ውድድር ፣ ተወዳዳሪዎች ራሳቸው በመረጧቸው እና ዳኞች በመረጡላቸው ሙዚቃዎች ሲፈተኑ ቆይተዋል።
በውድድር ሂደቱም በስምንት ሣምንታት ውስጥ አቅም ያላቸው ተወዳዳሪዎች በዳኞች አስተያየት ችሎታቸውን እያሻሻሉ፣ ለውጣቸውንም በግልፅ እያሳዩ ለነገው የፍፃሜ ውድድር አራቱ የተመረጡ ተወዳዳሪዎች ደርሰዋል።
“ፋና ላምሮት” በቀጥታ ስርጭት ሲካሄድ ከዳኞች ሙያዊ ዳኝነት በተጨማሪ ተመልካቾችም በ”8222” ላይ የተወዳዳሪዎችን ኮድ በመላክ ሲደግፉ መቆየታቸው ይታወሳል።
በነገው የባለተሰጥዖ ድምፃውያን ውድድር ላይም አድማጭ ተመልካቾች እንደቀደመው ሁሉ ያልተገደበ የ”ኤስኤምኤስ መልዕክቶቻቸውን” ከላይ በተጠቀሰው የአጭር የፅሁፍ መልዕክት ኮድ በመላክ ይገባዋል ለሚሉት ተወዳዳሪ ድምፃቸውን እንዲሰጡ ተጋብዘዋል፡፡
የምዕራፍ ዘጠኝ የፍፃሜ ተወዳዳሪዎች ፥ ረቂቅ አሰግደው፣ አሉላ ገብረ አምላክ፣ ዘላለም ታደሰ እንዲሁም መክብብ አራጌ በልዩ ዝግጅት እየተሰናዱ ይገኛል።
በፍፃሜው ውድድር ላይም ፥ 1ኛ ደረጃን ላገኘ የ200ሺህ ብር፣ 2ኛደረጃን ላገኘ 150 ሺህ ብር፣ 3ኛ ደረጃን ላገኘ 100 ሺህ ብር እንዲሁም 4ኛ ደረጃን ያገኘ ደግሞ የ50 ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል።
ፋና ቴሌቭዥንም አድማጭ ተመልካቾቹን ለማዝናናት ዝግጅቱን ማጠናቀቁ የተገለፀ ሲሆን፥ ነገ በቀጥታ ስርጭት ከቀኑ ስድሥት ሰዓት ጀምሮ የምዕራፍ ዘጠኝ የፍፃሜ ተፋላሚዎችን እየተመለከቱ እንዲዝናኑ ፣ ተወዳዳሪዎችንም ያልተገደበ የኤስኤምኤስ መልዕክት በመላክ እንዲደግፉ ፋና ቴሌቭዥን ጋብዟል።