ኤች አር 6600 በተግባር በኢትዮጵያ አለመረጋጋትን የሚያመጣና የሰላም ጥረትን የሚያደናቅፍ ነው – ፕሮፌሰር ጆን አቢንክ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአሜሪካ ኮንግረስ የቀረበው ኤች አር 6600 ረቂቅ አዋጅ በተግባር በኢትዮጵያ አለመረጋገትን የሚያመጣ፣ የሠላም ጥረትን የሚያደናቅፍ እና የዴሞክራሲ ልማትን የሚያቀጭጭ መሆኑን ፕሮፌሰር ጆን አቢንክ።
በሌይደን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ፖለቲካና አስተዳደር ትምህርት ፕሮፌሰር የሆኑን ጆን አቢንክ “ ዘ አሜሪካን ኮንሰርቫተቭ” ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ፥ ኤች አር 6600 ረቂቅ አዋጅ “በኢትዮጵያ መረጋጋትን፣ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን” የሚል ዓላማን ቢያሰፍርም በተግባር ውጤቱ የሚሆነው ግን ከዚህ በተቃራኒው መሆኑን ያብራራሉ።
ረቂቅ ህጉ በተመረጡ ኢትዮጰያውያን ላይ ማእቀብ እንዲጣል፣ ለኢትዮጵያ በፀጥታ ዘርፍ የሚሰጥ ድጋፍ እንዲታገድ እና ዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ)ን ከመሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ ፋይናንስ እንዳታገኝ አሜሪካ እንደምትከላከል የሚያደርግ ነው።
ፕሮፌሰሩ እነዚህ ሁሉ የረቂቅ ህጉ ምክር ሀሳቦች ግልፅ በሆነ አድሏዊ አካሄድ እና በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት በግልፅ ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንድትገባ የሚጠይቁ ናቸው ይላሉ።
ይህንንም ሲያስረዱ እርዳታን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት የፋይናንስ አቅሙ በፈቀደለት ልክ እየሰራ ለመሆኑ ረቂቅ ህጉ እውቅና እንደማይሰጥ፥ እንዲሁም ረቂቅ ህጉ ህወሃትንም ሆነ የፈፀማቸውን የጦር ወንጀሎች አንድም ቦታ ሳይጠቅስ ማለፉን ዘርዝረዋል።
ይህ መሆኑን አስቂኝ ያሉት ፕሮፌሰር ጆን አቢንክ፥ አርቃቂዎቹ ከህወሃተ ሰዎች ጋር ቁጭ ብለው የፃፉት ነው የሚመስለው ብለዋል።
ፀሃፊው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የተኩስ አቁም በማወጅ ከትግራይ ክልል ጦሩን ማስወጣቱን፥ ሆኖም ይህ የተኩስ አቁም በህወሃት ተቀባይነት አጥቶ የአማራና አፋር ክልሎችን በመውረር የፈፀማቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዘርዝረዋል፤ እንዲሁም ከዚህ ቀን በኋላም ምንም ዓይነት ጦርነት በትግራይ ክልል ላይ አለመደረጉንም አስረድተዋል።
ይህን ሁሉ ዘንግቶ አንዳች አሳማኝ ምክንያትን ማስቀመጥ የማይችለው ረቂቅ ህጉ ለዘማነት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ግኑኝነት የሚያበላሽ፣ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እና በሀገር ቤት የሚገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዘመዶቻቸውን የሚጎዳ ስለመሆኑ ነው የጠቀሱት።
እንደ ህግ ኤች አር 6600 የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ እና በዚያው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በጉዞ፣ በሀገር ውስጥ ፖለቲካ ተሳትፎ፣ በኢኮኖሚ እና ዓለም አቀፍ ብድሮች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ የሚያዝ ኢምፔሪሊስት የሆነ ህግ መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህ ሁኔታዎች ተደማምረው በኢትዮጵያ የከፋ ሁኔታን የሚፈጥር እንጂ ኮንግረሱ በረቂቅ አዋጁ ላይ አየዋለሁ የሚለውን መረጋጋት እና ለግጭት የሰላም አማራጭ እንዲሁም ዴሞክራሲን እንደማይሆን ነው የሚከራከሩት።
ይልቁንም የተረጋጋች፣ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት የሚሻ ከሆነ ኮንግረሱ ኢትዮጵያን በተመለከተ ሚዛናዊ አካሄድ ሊከተል፣ የግጭት ቀስቃሹን፣ ወራሪውን፣ በምርጫ የተቀመጠን መንግስት ለመጣል እና ሀገርን በጦርነት ለማመስ የተነሳውን ያወቀና የለየ አካሄድን ሊከተል ይገባል ሲሉ መክረዋል።
ፀሃፊው አሜሪካ ህወሃት ከጦረኝነት ወጥቶ ጠብመንጃውን እንዲያስቀምጥ እና ለሀገሪቱ ህግ ተገዢ እንዲሆን ግፊት ልታደርግ የሚገባበት ጊዜ አሁን መሆኑን በመጥቀስ ኢትዮጵያን በማእቀብ ማስጨነቅ ውጤት እንደማያፈራ አውቃ ያረቀቀውን ኤች አር 6600 ወደሚገባው ቆሻሻ መጣያ ትወርውረው ብለዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!