በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ጥቃት በደረሰበት ቦታ ላይ ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ ነው -የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት
አዲስ አበባ፣ መጋት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመሆን ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ገለጸ፡፡
የክልሉ መንግሥት መጋቢት 20 ቀን 2014 በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ቆርኬ/አውራ ጎዳና በጉዞ ላይ በነበሩ ሚሊሻና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በደረሰው ዘግናኝ ጥቃት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጿል፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሁለንትናዊ የብልፅግና ጉዟአችን በፅንፈኞች ሴራ አይደናቀፍም!
ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግላጫ
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መጋቢት 20 ቀን 2014 በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ቆርኬ/አውራ ጎዳና በሚባለው ልዩ ሥፍራ በምንጃር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች በጉዞ ላይ በነበሩት የህዝብ ሚሊሻና የፌዴራል ፖሊስ ላይ ባደረሱት ዘግናኝ ጥቃት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ፤ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸው በሙሉ መጽጽናናትን ይመኛል፡፡
ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለማጠናከርና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ በምንገኝበት በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ዉስጥ ይህን መሰል ዘግናኝ ድርጊት መፈጸሙ የጽንፈኞቸን እኩይ ዓላማና ተግባር ይበልጥ ያጋለጠ ነዉ፡፡
የነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች እኩይ ተግባርና ሴራ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ዘላቂ አብሮነትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞን ለማደናቀፍ የተወጠነ የጥፋት ዕቅድ አካል መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና የህዝቦች አብሮነት ጸር መሆናቸዉን በቅጡ ስለምንረዳ አምርረን የምንታገላቸውና ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጋር በመተባበር በህግ ፊት አቅርበን ተገቢና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሠራለን፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመሆን ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን እየገለጽን፣ መላው ህዝብ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!