Fana: At a Speed of Life!

በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶችና ማዕከላት በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ 2 ሺህ 111 ዜጎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች እና ማዕከላት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ 2 ሺህ 111 ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡

በዛሬው ዕለት ብቻ ከ1 ሺህ 420 በላይ ዜጎች ከሳዑዲአረቢያ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

በሳዑዲ አረቢያ ቁጥራቸው ወደ 750 ሺህ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን እንዳሉና፥ ከነዚህ ውስጥ 450 ሺህ ያህሉ በህገወጥ መንገድ የገቡ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ከ102 ሺህ የማያንሱ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ በተለያዩ የማቆያ ጣቢያዎች አስከፊ በሚባል ሁኔታ በእስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

መንግስት እየተከተለ ካለው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አኳያ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ዜጎችን ለመታደግ የተለያየ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ አሁን ዜጎችን ወደ ሀገር ማስገባት ጀምሯል፡፡

በዛሬው ዕለትም በጅዳ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ከ1ሺህ 430 በላይ ዜጎች ኢትዮጵያ ገብተዋል።

የጅዳ ተመላሾች አዲስ አበባ ሲደርሱም በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በርኦ፣ የስደት እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሃሰን፣ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኦንጋዬ ኦዳ፣ ኤምግሬሽንና እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ገምበቶ እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ÷ ዜጎችን ወደ ሀገር ለመመለስ በተቀመጠው እቅድ መሰረት ባለፉት ሁለት ቀናት እየተፈጸመ መሆኑን ጠቁመው÷ ዜጎችን በመመለስ ዘመቻውም እየተሳተፉ ያሉ የብሄራዊ ፈፃሚ ኮሚቴው አባል መስሪያ ቤቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተመላሾቹ አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ በተዘረጋው አሰራር መሰረት በማቆያ ማዕከል አንድ ቀን አርፈው ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እንደሚላኩ ጠቁመው÷ የማስመለሱ ስራ እስከ መጨረሻው በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፀም ከማዕከል እስከ ቀበሌ ያለው ቅንጅት የሰመረ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኦንጋዬ ኦዳ÷ ተመላሽ ዜጎች አዲስ አበባ ከደረሱ በኋላ መኖሪያቸው ደቡብ ክልል የሆኑትን ወደ ቀያቸው ለመውሰድ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.