በደቡብ ክልል ለምግብ እህል እጥረት ተጋላጭ ለሆኑ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ድጋፍ መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ለምግብ እህል እጥረት ተጋላጭ ለሆኑ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ከ87 ሺህ ኩንታል በላይ እህል ማሰራጨት መቻሉን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ጋንታ ጋሞአ በሰጡት መግለጫ÷ በ2013/14 የበልግ ወቅት ላይ ደቡብ ኦሞ እና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም አሌ፣ ደራሼ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ከ80 በመቶ በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው አንስተዋል፡፡
ጎፋ ዞን ውስጥ በሚገኙ 5 ወረዳዎች፣ የጋሞ ዞን ቆላማ ወረዳዎች፣ ወላይታ ዞን ቆላማ ወረዳዎች እና በክልሉ ማዕከላዊ ዞኖች ቆላማ ወረዳዎች ከፍተኛ የምርት ጉዳት መድረሱንም ጠቁመዋል።
በ2013/14 የምርት ዘመን በክልሉ ደቡባዊ አካባቢዎች ሰብል በአበባ ደረጃ ላይ እያለ የዝናብ እጥረት በመከሰቱ የምግብ ክፍተት መፈጠሩን ጠቁመው÷ ለአብነትም በደቡብ ኦሞ ፣ ኮንሶ፣ ጎፋ ዞኖች እንዲሁም የወላይታ እና የጋሞ ዞን ቆላማ አካባቢዎች ፣ አማሮ፣ ቡርጂ፣ አሌ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ላይ የሰብል ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡
ለምግብ እህል ክፍተት ተጋላጭ ለሆኑ ከ1ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ከ87 ሺህ ኩንታል በላይ እህል ማሰራጨት የተቻለ ሲሆን÷ በክልሉ የስነ ምግብ እጥረት አለባቸው ተብሎ ለተለዩ ከ305 ሺህ በላይ እናቶች እና ህጻናት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉም ተመላክቷል።
በክልሉ ከ127 ሺህ በላይ የሴፍቲኔት ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ቀለብ እንዲያገኙ መደፈረጉን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የተከሰተውን የመኖ እጥረት ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት እስከ 9 ሚሊየን ብር በመመደብ የመኖ ሳር ማቅረብ እንደተቻለ ገልጸው÷ የመኖ ልማት እና የውሃ አቅርቦት ስራ ማከናወን በመቻሉ በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን ሞት መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡