በጦርነት ለተፈናቀሉና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የጤና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነት ለተፈናቀሉ እና በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የጤና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጤና ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በሀገራችን ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች መከሰታቸውን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከባድ ችግር ተጋልጠዋል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ግብረኃይል ተቋቁሞ ከጤና ሚኒስቴር ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆን የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በአሁኑ ጊዜም በአፋር ክልል በ16 መጠለያዎች ከ294 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን፥ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይጋለጡ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 63 ሺህ ለሚሆኑት የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፉ እንደተደረገላቸው በመግለጫው ተመልክቷል።
120 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ የኮሌራ ኩፍኝ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ክትባት ተሰጥቷል ነው የተባለው።
ለአጥቢ፣ ለነፍሰ ጡር እና ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት በምግብ እጥረት እንዳይጎዱ 30 የሚሆኑ ተንቀሳቃሽ የጤና እና በስርዓተ ምግብ ባለሞያዎች የተደገፈ ጊዜያዊ ክሊኒክ በማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ከ1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 130 ሺህ የሚሆኑት መሰረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርገዋል።
በክልሉ 53 የሚሆኑ ተንቀሳቃሽ የጤና እና ሥርዓተ ምግብ አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን፥ በአጋር ድርጅቶች እየተደገፈ ተጨማሪ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት።
ከ600 በላይ የሥነ አዕምሮ ባለሙያዎች ወደ ክልሉ እንዲሄዱ ተደርጎ 10 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች የሥነ አዕምሮ ሕክምና እና የሥነልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን ዶክተር ደረጀ አንስተዋል።
ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው የሕክምና እና የህግ ድጋፍ እንዲያገኙ ማዕከላት ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሶማሌ ክልል፣ በኦሮሚያ የተወሰኑ ዞኖች፣ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ ለመመከት እና በዜጎች ላይ ከፍተኛ የጤና እክል እንዳያደርስ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል።
ወረርሽኝ እንዳይከሰት ለመከላከል በሶማሌ ክልል 196 ሺህ እና በኦሮሚያ 424 ሺህ ዜጎች የኩፍኝ እና የኮሌራ ክትባት ተሰጥቷል።
በተደረገው ጥናትም ድርቅ በተከሰተባቸው ክልሎች 14 በመቶ ለምግብ ዕጥረት የተጋለጡ ህፃናት መኖራቸውን በጥናት መለየቱን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ነገር ግን በድርቅ ምክንያት ምንም የሰው ህይወት አልጠፋም ነው ያሉት።
በትግራይ ክልልም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን እና አስፈላጊውን አቅርቦት ከዓለም የጤና ድርጅት እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን እየቀረበ ይገኛል ነው ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፡፡
በተለይ ለወባ፣ ቲቢ እና ሌሎች በሽታዎች በየቀኑ የመድሀኒት አቅርቦት በአውሮፕላን እየደረሰ መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል።
ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩም ነው በመግለጫው የተመለከተው፡፡
በተጨማሪም ከሳዑዲ አረቢያ ለሚመለሱ ዜጎች አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት በጤና ተቋማት እየታገዘ መሆኑን በመግለጫው አንስተዋል።
በምንይችል አዘዘው