ኮርፖሬሽኑ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በስፋት በአገር ውስጥ ለማምረት እየሰራ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በስፋት ለማምረት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችንበአገር ውስጥ በስፋት ለማምረት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ዮናስ አያሌው ÷ከመሰረታዊ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ውጪ ያሉ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ አምርቶ ለመጠቀምና ዘርፉን ለማሳደግ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በማምረት የዳበረ ልምድ ካለው ከራይዚንግ ሆንግፋ ግሩፕ ኩባንያ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ የትኞቹ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና ማምረቻ ፋብሪካዎች እንደሚያስፈልጉ የተለዩ ሲሆን÷ ጎማን መልሶ መጠቀም፣ የአሉሙኒየምና የተለያዩ የኮንክሪት ምርቶችን ማምረት የሚችሉ ፋብሪካዎች በመትከል ከውጪ የሚገቡ ግብዓቶችን ለማስቀረትና ግንባታዎችን ከተቀመጠላቸው ቀነ ገደብ አስቀድሞ አጠናቆ ለማስረከብ እንዲቻል እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ዕቅዱን እውን ለማድረግ የተሻለ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ስርዓት ተግባራዊ ተደርጓል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው÷ የስልጠናና የልህቀት ማዕከል ግንባታ ተጠናቀው የግብዓት ማምረቻ ማዕከል እንደገና የማደራጀትና የግብዓት ማምረቻ ፋብሪካዎችን ለመትከል የሚያስችሉ የመሰረተ ልማቶች ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
አስፈላጊ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት የወጪ ምንዛሬን ለማዳን እና ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር ያለውን ጠቀሜታ ማስረዳታቸውንም ከኮርፖሬሽኑያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከተቋሙ ጋር በጋራ እየሰራ የሚገኘው የራይዚንግ ሆንግፋ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሪታን ሲንግ በበኩላቸው÷ ኩባንያቸው የኮንስትራክሽን ግብዓት በማምረት ትልቅ ልምድ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስለሆም ጎማን መልሶ በመጠቀም፣ የአሉሙኒየም ግብዓቶችን በማምረት፣ የኮንክሪት የግድግዳ ፓኔሎች፣ ቱቦዎችና ሩፍ ታይልስ እንዲሁም በመንገድ ቅብና በሌሎች ተያያዥ የኮንስትራክሽን ግብዓቶት አመራረት ዙሪያ ሰፊ ልምድ ለኮርፖሬሽኑ ከማካፈል በተጨማሪ የቴክኖሎጂ አማራጮች የሚቀርቡበትን እድል ለመፍጠር በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡