የጉምሩክ ኮሚሽን የምግብ ሸቀጦችን ከውጭ ለሚያስገቡ ፈጣን አገልግሎት እሰጣለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ለሚያስገቡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳር ፣ የህጻናት ወተት እና ሩዝ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ በጉምሩክ ኮሚሽን በቀጥታ እንዲገቡ መወሰኑን ተከትሎ ኮሚሽኑ የዚህ እድል ተጠቃሚ ለሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት መዘርጋቱንና አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን የሕግ ተገዥነት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ ገልጸዋል፡፡
በዘርፉ የሚሰማሩ አካላት በጉምሩክ ኮሚሽን ዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ እንደሚሰጣቸው ጠቅሰው÷ ፈቃዱን ካገኙ በኋላ በኮሚሽኑ ስር በሚገኙ እና በመረጡት 18 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በኩል መስተናገድ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ፈቃድ ለማግኘት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡
ሸቀጦቹ ከጉምሩክ ወደብ ከተነሱ በኋላ በአግባቡ ለተጠቃሚው እንዲደርሱ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ገልጸው÷ በተለይም ህብረተሰቡ ከመንግስት የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ህገወጦችን ማጋለጥ ይገባዋል ብለዋል፡፡
መሰረታዊ የምግብ ሽቀጦች ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ ከሚያስገቡት አካላት በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የምንዛሬ ፈቃድ አግኝተው በዘርፉ ለተሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡