በአዳማ ከተማ የሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት 250 ፕሮጄክቶች እየተሰሩ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዳማ ከተማ ከነዋሪዎች የሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት 250 ፕሮጄክቶች በመሰራት ላይ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘርፉ አስፋው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ከመንግሥት በተገኘ 1 ቢሊየን ብር እና ከህብረተሰቡ በተዋጣ የ400 ሚሊየን ብር እንዲሁም ከሌሎች ምንጮች በተገኙ ገቢዎች ነው ፕሮጄክቶቹ እየተገነቡ የሚገኙት፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች የአዳማ የመንገድ ዳር መብራቶች ከተማዋን የማይመጥኑ እና በምሽት ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ሁኔታ የፈጠሩ እንዲሁም ለደኅንነት ስጋት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ዘርፉ አስፋው በበኩላቸው የመንገድ ዳር መብራቶች ብልሽት የሚገጥመው ከስርቆት፣ ከብልሽትና ከአገልግሎት ጊዜ ማብቃት ጋር በተያያዘ መሆኑን ጠቁመው÷ ለመፍትሄው የጥገናና የግንባታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡
ችግሩ በተለያዩ አካባቢዎች መከሰቱን የገለጹት ስራ አስኪያጅ÷ ለመፍትሄው የጥገናና አዳዲስ የመንገድ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በከተማዋ በሚገኙ መጋዘኖች አካባቢ የከባድ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መበራከት ለተደጋጋሚ የመንገድ ብልሽት ምክንያት መሆኑን ጠቁመው÷ መፍትሄ ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን እያጤው መሆኑን ገልጸዋል።
በአፈወርቅ እያዩ