የለገዳዲ ክፍል ሁለት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጄክትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 860 ሺህ የከተማዋን ነዋሪዎች የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርገው የለገዳዲ ክፍል ሁለት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጄክትን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ገለጸ።
በባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰርካለም ጌታቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ÷ ከሁለት ዓመታት በፊት የተጀመረው እና በ4 ቢሊየን ብር በጀት እየተገነባ ያለው ፕሮጄክት ከሁለት ወራት በኋላ ይመረቃል።
በአሁኑ ወቅትም 72 ኪሎ ሜትር የውሃ ማሰባሰቢያ ፣ 68 ኪሎ ሜትር ውሃውን ወደየመንደሩ የሚወስድ እና እያንዳንዳቸው ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃን በየቀኑ መያዝ የሚችሉ የውሃ ጉድጓዶች ግንባታ ተጠናቋል ብለዋል።
ፕሮጄክቱ የጉለሌ እና የየካ ክፍለ ከተሞች ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋልም ተብሏል።
ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም የውሃ አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ የፈረቃ ውሃ ተደራሽነት ጊዜን እንደሚያሳጥር አመላክተዋል።
ሌሎች የግንባታ ፕሮጄክቶችንም በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በትእግስት አብርሀም