በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ35 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ35 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ባቡር ፌርማታ ላይ በፖሊስ አባላት በተደረገ ፍተሻ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልደታ ባቡር ፌርማታ ላይ የተያዘው ዶላር 35 ሺህ 600 የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡
አንዲት ግለሰብ በቦርሳዋ ዶላሩን ይዛ በባቡር ለመሳፈር ስትገባ በወቅቱ በፌርማታው ላይ ተመድበው ስራቸውን ሲያከናውኑ የነበሩት የፖሊስ አባላት ባደረጉት ፍተሻ እንደተያዘም ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የፖሊስነት ተግባር በታማኝነትና በአገልጋይነት ስሜት የሚከወን ሀላፊነት በመሆኑ ይህንን ተግባር ለተወጡ ፖሊስ አባላትም ምስጋና አቅርቧል፡፡
ሰዎች የውጭ ሃገራት ገንዘቦችን ይዘው ለመንቀሳቀስ እና በእጃቸው ለማቆየት በብሄራዊ ባንክ መመሪያ ከተፈቀደው መጠን እና የጊዜ ገደብ ውጪ መመሪያውን ጥሰው የሚገኙ ግለሰቦች በህግ አግባብ ተጠያቂ ይሆናሉም ነው ያለው።
ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ መቅረቡን ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡