የህብረት ሥራ ማህበራት ለገጠር ልማት ያላቸውን ሚና ለማጠናከር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን የህብረት ሥራ ማህበራት በገጠር ልማትና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ያላቸውን ሚና ለማጠናከር እየተሰራ ነው አለ።
2ኛው ሀገር አቀፍ የህብረት ሥራ ሪፎርም የንቅናቄ መድረክ “ወደ ቀበሌ መድረስ” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ከተሞች መካሄድ ጀምሯል።
የንቅናቄ መድረኩ በአዳማ፣ ሀዋሳ፣ አሶሳ፣ ጅማ ፣ ጅግጅጋ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡
በአዳማ በተጀመረው የንቅናቄ መድረክ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌትነት ታደሰ ፥ የህብረት ሥራ ማህበራትን በቀበሌ ደረጃ ለማዳረስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በገጠር ልማትና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ያላቸውን ሚና ለማጠናከርም የንቅናቄ ዘመቻ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በኮሚሽኑ ስር 26 ሚሊየን አባላትን የያዙ ከ89 ሺህ በላይ መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማህበራት መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡
ለ8 ቀናት በሚቆየው የንቅናቄ ዘመቻ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ4 ሺህ በላይ የህብረት ሥራ የልማት አመቻቾች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ በበኩላቸው ፥ የህብረት ሥራ ማህበራት አደረጃጀት በገጠር ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለመፍጠር ቁልፍ መሠረት የሚሆን የመደመር መንገድ መሆኑን አንስተዋል ።
በግዛቸው ግርማዬ