Fana: At a Speed of Life!

በብሔር እና በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ የሚያሰራጩ 111 ሕገ ወጥ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መኖራቸውን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምንም ዓይነት የብሮድካስት ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚንቀሳቀሱና የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያናጉ በብሔር እና በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ የሚያሰራጩ 111 ሕገ ወጥ የበይነመረብ መገናኛ ብዙኃን መኖራቸውን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የፌደራል ፖሊስ ሕገ ወጥ የበይነመረብ መገናኛ ብዙኃንን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ÷ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሰረት ምንም ዓይነት የብሮድካስት ፈቃድ ሳይኖራቸው የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያናጉ በብሔር እና በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ የሚያሰራጩ እንዲሁም በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መንግስትና ሕዝብን ለመለያየት ሌት ተቀን የሚሰሩ 111 ሕገ ወጥ የበይነመረብ መገናኛ ብዙኃን መኖራቸውን ነው ያስታወቀው፡፡

ከነዚህ ሕገ ወጥ የበይነመረብ መገናኛ ብዙኃን መካከል በጣም ወጣ ያሉ ብሔርን ከብሔር ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው ያላቸውን 10 ተጠርጣሪዎች ለይቶ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ፌደራል ፖሊስ በዚሁ መግለጫው÷ ህብረተሰቡ ያገኘውን መረጃ ሁሉ ከመጠቀም በመቆጠብ በጥንቃቄ መርምሮ ማየትና ማገናዘብ እንዳለበት አሳስቦ÷ በሕገ ወጥ መንገድ በበይነመረብ መገናኛ ብዙኃን አማካይነት አጀንዳ ቀርፀው በሃይማኖት እና በብሔር ህብረተሰቡን ለማጋጨት የሚሰሩ አካላትን በማጋለጥና ለሕግ አሳልፎ በመስጠት ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታና የፍትሕ አካላት ጋር በመቀናጀት የጀመረውን የሕግ ማስከበር ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቀው፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ሕገ ወጥ የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃንን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሰረት ምንም ዓይነት የብሮድካስት ፍቃድ ሳይኖራቸው የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የሚያናጉ በብሔር እና በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ግጭት ቀስቃሽ መረጃ የሚያሰራጩ እንዲሁም በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መንግስትና ህዝብን ለመለያየት ሌት ተቀን የሚሰሩ 111 (አንድ መቶ አስራ አንድ) ሕገ ወጥ የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸውን ባሰባሰበው መረጃ አረጋግጧል። ከዚህ ውስጥ በጣም ወጣ ያሉ ብሔርን ከብሔር ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱትን ለይቶ 10 (አስር) ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራባቸው ይገኛል።

እነዚህ ግለሰቦች የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ አጀንዳዎችን በመቅረጽ የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት እንዳይረጋጋ የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት በብሔር እና በሀይማኖት መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር ሲያደርጉ የቆዩ መሆናቸው ይታወቃል።

ተቋሙ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ክትትል ግለሰቦቹ ምንም አይነት ህጋዊ ፍቃድ የሌላቸውና በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013 መሰረት ያልተመዘገቡ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ባሰባሰበው መረጃ ማረጋገጥ ችሏል። ግለሰቦቹ የሚዲያ ተከታዮቻቸውን በመጠቀም ሐሰተኛና ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን የሚያሰራጩት በክፍያ እንደሆነም በምርመራ ደርሶበታል።

በየትኛውም ሚዲያ ተጠቅመው መረጃን ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርጉ ግለሰቦች የሀገሪቱን ህግና ሥርዓት አክብረው መንቀሳቀስ እና ህጋዊ መስመር በመከተል በተጠያቂነት መንፈስ መስራት ይኖርባቸዋል።

ፖሊስም ህግን አክብረው በማይሰሩት ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ ይወዳል፡፡

በመጨረሻም ህብረተሰቡ ያገኛውን መረጃ ሁሉ ከመጠቀም በመቆጠብ በጥንቃቄ መርምሮ ማየትና ማገናዘብ እንዳለበት እያሳሰበ በህግ-ወጥ መንገድ በበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት አጀንዳ ቀርፀው በሀይማኖት፣ በብሔር ህብረተሰቡን ለማጋጨት የሚሰሩ አከላትን በማጋለጥና ለህግ አሳልፎ በመስጠት ሀገራዊ ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሰሞኑን ለህዝብ ሲገለጽ እንደነበረው ከሌሎች የጸጥታና የፍትህ አካላት ጋር በመቀናጀት የጀመረውን የህግ ማስከበር ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታውቃል።

 

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.