Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ሥራ ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ በዛሬው ዕለት ተመርቆ ሥራ ጀምሯል፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያው÷ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በትብብር የተሰራ መሆኑ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ጁሃር በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በ104 ነጥብ 5 ሞገድ የሚደመጠው የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ሬዲዮ ሥራ መጀመሩ በዩኒቨርሲቲውና በማህበረሰቡ መካከል የበለጠ መቀራረብ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል፡፡
ለከተማ አስተዳደሩም ቢሆን ሃሀገራዊና ወቅታዊና ልማታዊ ጉዳዮችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ከድሬ ሬዲዮና ከሃሮማያ ፋና ኤፍ ኤም በመቀጠል አማራጭ የመረጃ ምንጭ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አማራጭ ሚዲያ መገንባቱ ለህብረተሰቡ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው÷ አስተዳደሩም ለጣቢያው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይሰራል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ እና ኤፍ ኤም ሬዲዮ ከማህበረሰቡ ጋር ለመድረስ ሲሠራ የነበረውን ሥራ አጠናቆ ዛሬ በይፋ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ለድሬዳዋ እና ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ግንባታው እንዲሰራ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት መፈጸሙንም ገልጸዋል፡፡
ፋና ወደ ማህበረሰቡ ወርዶ የሚሠራቸው በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ የቴክኒክና ሌሎች ህብረተሰቡን ሊጠቅሙ የሚችሉ የይዘትና የሙያ ድጋፍ እንደሚያደርግም አመላክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ይህንን ትልቅ ኃላፊነት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዲወስድ ስላደረገ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የሬዲዮ ጣቢያው በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮችን ለህብረተሰቡ በተገቢው ሁኔታ ለማድረስ ሚናው ከፍ ያለ ነውም ብለዋል።
አክለውም ፋና ከመገንባት ባለፈ የቴክኒክ፣ የአቅም ግንባታ እንዲሁም ይዘት ላይ እገዛ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።
የሬዲዮ ጣቢያው የስቱዲዮ እና የስርጭት አንቴና ስራ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ነው የተገነባው፡፡
የሬዲዮ ጣቢያው በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በሶማሊኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች እንደሚደመጥ ተጠቁሟል።
በዮሐንስ ደርበው እና ሃይማኖት ኢያሱ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.