Fana: At a Speed of Life!

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ካሉብ እና ሂላላ አካባቢዎች ለሚገኙ ማኅበረሰቦች ልማት የሚውል 113 ሚሊየን ብር አበረከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በሶማሌ ክልል ካሉብ እና ሂላላ አካባቢዎች ላሉ ማኅበረሰቦች ልማት የሚውል 113 ሚሊየን ብር አበርክቷል ።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ ካሉብ ተገኝተው የገንዘብ ርክክብ ሲያደርጉ እንደተናገሩት፥ በአካባቢው በሚከናወን የነዳጅ እና የጋዝ ማዉጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች በገቡት ስምምነት መሰረት ላለፉት አምስት ዓመታት ለማኀበረሰቡ የሚያስፈልጉ የልማት ሥራዎች በስምምነቱ መሰረት አልፈጸሙም፡፡

በመሆኑም የእነዚህን ዓመታት 113 ብር ሚሊየን ለክልሉ በማስረከብ የአካባቢው ነዋሪዎችና የክልሉ መንግስት በመነጋገር በአካባቢው የተጓደሉ የልማት ስራዎችን እንዲያከናውን ይደረጋል ብለዋል ።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ እና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በተገኙበት የገንዘብ ርክክብ ላይ የአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ የልማትና መሰል ጥያቄዎች አንስተዋል ።

የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ቀደም ሲል በአካባቢው በርካታ ኩባንያዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀናጅቶ የመሥራት ችግር ነበረባቸው ብለዋል፡፡

የነዳጅ ማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩ ኩባንያዎች በገጠማቸው የገንዘብ ችግር አቋርጠው ለመውጣት መገደዳቸውንም የተናገሩት ሚኒስትሩ፥ ሥራዎች በሚፈለገው ልክ እየተሰሩ እንዳልሆነም ነው የገለፁት።

አሁን የቀረው “ፖሊ ጂ ሲ ኤል” የተባለ የቻይና ኩባንያ እንደሆነና ወደ ሥራ እንዲገባ ከተሰጠው የ6 ወር ጊዜ ውስጥ አምስቱ አጥጋቢ ሥራ ሳይሰራበት እንዳጠናቀቀውም ጠቁመዋል፡፡

በፀጋዬ ወንድወሰን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.