በኢትዮጵያ 53 ቋንቋዎች የአጻጻፍ ስርዓት ተበጅቶላቸው ለመማር ማስተማር ውለዋል- ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ 53 ቋንቋዎች የአጻጻፍ ስርዓት ተበጅቶላቸው ለመማር ማስተማር መዋላቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሁለተኛው አገር አቀፍ የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ጉባኤ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ከ80 በላይ ቋንቋዎች ውስጥ 53ቱ ቋንቋዎች የአጻጻፍ ስርዓት ተበጅቶላቸው ለትምህርት አገልግሎት መዋላቸውንና በቀጣይም የቋንቋዎቹን ቁጥር ለመጨመር መታሰቡን ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የጸደቀውን የቋንቋ ፖሊሲ መሰረት በማድረግ የቋንቋ ትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን ለማሳደግና ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴርና ከስምንት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ላለፈው አንድ ዓመት በጉዳዩ ላይ የዳሰሳ ጥናት ማድረጉንም ተናግረዋል።
በጥናቱ ምክረ ሀሳብ አማካኝነት የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን ለማዳበርና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚያስችል መነሻ ስርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
ጉባኤው የቋንቋዎች ትርጉምና አስተርጓሚነት ለአገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ያለው ፋይዳና ለመንግስት የቋንቋዎች ፖሊሲ ግብአት የሚውሉ ሃሳቦችን ለማሰባሰብ እንደተዘጋጀ ተነግሯል።
ቋንቋዎች ልማት እንዲሁም የትርጉምና አስተርጓሚነት ሙያን ማጎልበት በቀጣይ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሚሆን መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!