Fana: At a Speed of Life!

 በቦሌ ክፍለ ከተማ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ 3 የዳቦ ፋብሪካዎችን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እንዲያስችል በክፍለ ከተማው በሚገኙ 3 ወረዳዎች የሚገነቡት የዳቦ ፋብሪካዎች ግንባታ በባለሀብቶች ድጋፍ የሚሰሩ ናቸው ተብሏል።

በግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ሺፈራው እንደተናገሩት÷መንግሥት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መካከል የዳቦ አቅርቦትን በማሳደግ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አንዱ ነው፡፡

ግቡን ለማሳካት ባለሀብቶች ክፍለ ከተማው ያቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ለሰጡት ፈጣን ምላሽም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ  አመስግነዋል፡፡

እንደቀደሙት ዓመታት የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ ያለግንባታ ዓመታት የሚቆጠሩበት ጊዜ እንደማይቀጥል ጠቅሰው÷ የዳቦ ፋብሪካዎቹ ግንባታ በሁለት ወራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ነው የተናገሩት።

ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ በመግባት ግንባታውን እንዲያከናውኑ ማሳሰባቸውንም ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የክፍለ ከተማው አመራሮችና ነዋሪዎች ለባለሀብቶቹ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.