በደቡብ ክልል ከ152 ሺ ኩንታል በላይ ስንዴ በበጋ መስኖ መልማቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ሰኔ 6፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በደቡብ ክልል ከ152 ሺ ኩንታ በላይ ስንዴ በበጋ መስኖ ማልማት መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል፡፡
በደቡብ ክልል በ2014 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም እና በ2015 እቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እየተካሔደ ነው።
በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩሩ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት፥ በክልሉ ከ5ሺ ሄክታር በላይ መሬት በማረስ ከ152 ኩንታል በላይ ስንዴ በበጋ መስኖ ማልማት ተችሏል።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፥ አርሶ አደሩን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ከክልል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር የአመራሩ እና የባለሙያው ጥረት ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በተለይ ዘንድሮ ስንዴን በበጋ መስኖ ለማልማት የተደረገው ጥረት በመላው አርሶ አደር ዘንድ የፈጠረው የቁጭት ስሜት ለቀጣዩ ዓመት ስራችን ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት፡፡
ያሉንን ጸጋዎች በመለየት ወደ ስራ ተገብቷል ያሉት አቶ ኡስማን÷ ከድህነት መውጣት እንዲቻል የፍራፍሬ፣የዶሮ እና የቅመማ ቅመም መንደር በመመስረት ለተሻለ ለውጥ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራን ስኬታማ ለማድረግ ከችግኝ ዝግጅት እስከ ተከላ ባለው ሂደት የተገኘው ውጤት ለግብርና ስራ ምቹ መደላድል መፍጠሩንም ጠቁመዋል።
በክልሉ ከ290 ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተቀናጀ ተፋሰስ ለማልማት ታቅዶ ወደ ተግባር የተገባ ሲሆን፥ የእቅዱን 94 በመቶ ማከናወን ተችሏል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡