Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል በሲሚንቶ አቅርቦት ላይ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ምክክር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 6፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በሶማሌ ክልል በሲሚንቶ አቅርቦት ላይ ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ያለመ ምክክር ተካሄደ፡፡

በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን÷ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ያልተሰሩ የተከማቹ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው÷ ከለውጡ በኋላ በተገኘው የተረጋጋ ሰላም የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመረዳት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሰጠው አቅጣጫ መሰረት በክልሉ የሚገኙ ፕሮጀከቶች ቅድሚያ የሚያገኙበትን የአሰራር ስርዓት እንዲዘረጉ አሳስበዋል።

የሲሚንቶ ፋብሪካ ተወካዮች በበኩላቸው÷ በክልሉ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ እንደሚያደንቁ ገልፀው÷ ለተከሰተው የሲሚንቶ እጥረት መፍትሔ ለመስጠት ከክልሉ ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።

በምክክር መድረኩ ላይ÷ በሶማሌ ክልል 25 የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች፣ ከ10 በላይ ሆስፒታሎች፣ 11 አዳሪ ትምህርት ቤቶች፣ የውሀ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀከቶች በግንባታ ላይ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፥ በ2014 በጀት ዓመት ማለቅ የነበረባቸው 240 ፕሮጀክቶች በሲሚንቶ እጥረት የተነሳ ወደ 2015 በጀት ዓመት መሸጋገራቸውም ተመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.