የኒውክሌር ኃይል ልማትን የተመለከተ አገር አቀፍ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኒውክሌር ኃይል ልማትን የሚመለከት አገር አቀፍ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ ላይ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ከቱርክ፣ ከኮሪያ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨሪሲቲ፣ ከማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የዘርፉ አስተባባሪ ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም ብሔራዊ የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ግብረ ኃይል አባላት እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ÷ ኢትዮጵያ እኤአ ከ1957 ጀምሮ ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ተቋም ጋር ኒውክለርን ለሰላማዊ አገልግሎት ለማዋል በልዩ ልዩ የኒውክሌር ሳይንስ ዘርፎች እና ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰራች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ያለውን አገራዊ አቅም ለማጎልበት እና ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ ሁለገብ ተግባራትን እያከናወነች መሀኗንም ተናግረዋል።
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው የቴክኖሎጂ ፕሮግራሞች አንዱ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ማዋል ነው ያሉት ዶ/ር ባይሳ÷ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ሳይንስ ቴክኖሎጂን ባካተተ መልኩ የኒውክሌር መርሐ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም መያዟን ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ተቋም የኒውክሌር ፕሮግራምን በኢትዮጵያ ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነትና እያደረገ ላለው የቴክኒክ ድጋፍ አመስግነዋል።
ለፕሮግራሙ ትግበራ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው÷ አገር አቀፍ የሰው ሃይል ዳሰሳ ጥናት ተጠናቆ የአቅም ግንባታ ስራው ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የብሔራዊ የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ግብረ ኃይል አስተባባሪ ኢንጂነር አበባ ጌጡ በበኩላቸው÷ ለኒውክሌር ቴክኖሎጂ ትግበራ ብሔራዊ የሰው ሀብት ላይ የተጠናውን የዳሰሳ ጥናት ውጤት ለመድረኩ አብራርተዋል።
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የኒውክሌር ኢንጂነር መህመት ሴይሃን በበኩላቸው፥ ዘርፉን ለማሳደግ ደረጃ አንድ የኒውክሌር ኃይል ልማት ቁልፍ ጉዳዮችን የተመለከተ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
በመድረኩ ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች በቀጣይ ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡