በህልውና ዘመቻው ለተሳተፉ የጎንደር ከተማ ጤና ባለሙያዎች እውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ በህልውና ዘመቻው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎች ፣ የአምቡላንስ ሹፌሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባዘጋጀው መርሃ-ግብር የከተማው ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ÷ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ ሀገር በጠላት እንዳትወረር በሙያችሁ ላደረጋችሁት ሀገራዊ አበርክቶ ምስጋና እና ዕውቅና ይገባችኋል ሲሉ ባለሙያዎችን አመስግነዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ በለጠ ፈንቴ ÷ በህልውና ዘመቻው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ 43 የጤና ባለሙያዎች፣ አምሥት የአምቡላንስ ሹፌሮች እና ሥምንት ጤና ጣቢያዎች ዕውቅና መሠጠቱን ተናግረዋል፡
ኃላፊው አክለውም ሁለት የዕርዳታ ድርጅቶች ፣ የጎንደር ደም ባንክ ፣ ጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፣ ለመድሃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ እና ለግል ጤና ተቋማት ዕውቅና እንዲሁም የዋንጫና የምስጋና የምስክር ወረቀት መሠጠቱንም ጠቁመዋል፡፡
በአበራ መኮንን