Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ በነገው ዕለት በሚያካሂደው ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳልፋል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን በነገው ዕለት ያካሂዳል።

በነገው ዕለት በሚያካሂደው ስብሰባም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በመደበኛ ስብሰባው የ2012 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት የተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራም ነው የሚጠበቀው።

እንዲሁም በኢትዮጵያ እና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ለሁለተኛው ሃገር አቀፍ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና ሃይጂን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች ይመራል።

በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በኮሪያ ኤክስፖርት – ኢምፖርት ባንክ መካከል ለአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል መመስረቻ ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እንዲሁም በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በሳዑዲ የልማት ፈንድ መካከል ለደብረ ማርቆስ – ሞጣ የመንገድ ስራ ማሻሻያና ማሳደጊያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመራ ይሆናል።

በተመሳሳይ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙር እና የአፍሪካ ቀን ረቂቅ አዋጅ፣ የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የወጣ የነጠላ ኦዲት ረቂቅ አዋጅ፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሠራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ እና የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀ ረቂቅ ደንብን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች እንደሚመራ የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.