ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ስኬት የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው – የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑንን ውጤታማ በማድረግ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የሃይማኖት አባቶች እንደገለጹት÷ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማነት በሀገር ሰላም፣ ደኅንት፣ ፍቅር እና አንድነትን ያስቀደሙ ጉዳዮች ላይ መስራት ይጠበቅብናል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ የሃይማኖት አባት መላከ ምህረት ቆሞስ አባሲኖዳርጋ በዳዳ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ካለችበት ፈተና የሚያሻገር በመሆኑ ለውጤታማነቱ የሃይማኖት ተቋማቱና አባቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡
ሼህ ሙሀመድ የሱፍ በበኩላቸው አገራዊ ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች ወደ ሕዝቡ ወርደው መስራት እና ምዕመኑ አርአያ እንዲሆን ማስቻል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ሕዝቡን ማስተማርና በምክክር የሚፈቱ ጉዳዮችን ለኮሚሽኑ በማቅረብ ችግሮች የሚፈቱበትን መፍትሔ በማቅረብ እንዲሁም በንቃት እንዲሳተፍ በማድረግ በኩል አባቶች ኃላፊነት እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡
መምህር አስፋው ሽፈራው በበኩላቸው÷ የሃይማኖት አባቶች ትውልድን መቅረፅ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት እና አባቶች የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስቀጥሉ ጉዳዮች ላይ መስራት ከቻሉ የምክከር ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ውጤት ማምጣት እንደሚችልም አመላክተዋል፡፡
አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ግቡን እንዲያሳካም ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንዳለበት የገለጹት ሃይማኖት አባቶቹ÷ የምክከር ኮሚሽኑ ለዘመናት የነበሩብንን ችግሮች በመፍታት ኢትዮጵያ አሁን የምትፈልገውን እና መሆን የሚገባትን እንዲሁም ማግኘትን ያለባትን ሰላም እንድታገኝ ያግዛል ብለዋል፡፡