የኮሜሳ አንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት ማስጀመሪያ ስብሰባ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመጀመሪያው የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ(ኮሜሳ)የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት ማስጀመሪያ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡
በስብሰባው ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያማከለ የአሰራር ማሻሻያ ግምገማ፣ ጥናታዊ ሪፖርት፣ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፎች እና የኮሜሳ የአንድ መስኮት ኤሌክትሮኒክ አገልግሎት የልማትና የትግበራ ስትራቴጂ ረቂቅ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በዲጂታል ግንኙነቱ ዘርፍ ያለው የቴክኖሎጂ አቅርቦት የደረሰበረት ደረጃ ላይ ገለጻ እንደሚኖር የተመላከተ ሲሆን÷ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና አጋሮቻቸውም ተሞክሮዎቻቸውን ያካፍላሉ ተብሏል፡፡
መድረኩን የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ÷ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ማስጀመራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የ“ኮሜሳ” የሚኒስትሮች ምክር ቤት በፈረንጆቹ ሕዳር 2017 ባካሄደው 37 ኛው የአባል ሀገራቱ ስብሰባ ላይ የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት ለማስፋፋት መወሰኑ ይታወሳል።
ውሳኔው የተላለፈውም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ተዋናዮችን በቀጠናው ሀገራት ካሉ የመንግስት ኤጀንሲዎች እና የግል ባለድርሻ አካላት ጋር ለማቀናጀት እና ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ የግብይት እና የመረጃ ግንኙነት ምኅዳር ለመፍጠር ነው።
በአዲስ አበባ የተጀመረው የቀጣናው ሀገራት ስብሰባ የፊታችን ሐምሌ 13 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡