Fana: At a Speed of Life!

ከ300 ሺህ በላይ ቤቶች ለአቅመ ደካማ ዜጎች ተገንብተዋል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ ለሆኑ አቅመ ደካማ ዜጎች ከ300 ሺህ በላይ ቤቶች ተገንብተዋል አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፡፡
ሚኒስትሯ የ2018 በጀት ዓመት ሦስተኛው የ100 ቀናትና የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ግምገማን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ የነበሩባትን ስብራቶች በመጠገን በፖለቲካውም ሆነ በማህበራዊ ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበች ነው ብለዋል፡፡
ማንኛውም የልማት ሥራ ውጤቱ የሚለካው በሰው ላይ በሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ መሆኑን ገልጸው፥ ከዚህ አኳያ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችንና አረጋውያንን ቀዳሚ ተጠቃሚ ለማድረግ መሰራቱን ተናግረዋል።
ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በብድርና ቁጠባ ተደራጅተው ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ ይህም ዜጎች ከተረጂነት ወጥተው በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በመሳተፍ ኢኮኖሚው ላይ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በሰው ተኮር ሥራዎች ረገድ ለአቅመ ደካማ ዜጎች ከ300 ሺህ በላይ ቤቶች እንዲገነቡ መደረጉን አስታውሰው፥ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ24 ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በ14 የተለያዩ ዘርፎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማሳተፍ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በዚህም የመንግስትንና የሕዝብን 54 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን የተቻለ ሲሆን፥ የበጎ ፈቃድ ሥራ ባሕል እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ዜጎችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር በተሰሩ ስራዎች ቀደም ሲል 27 ሚሊየን የነበረው የተረጂ ዜጎች ቁጥር ወደ 3 ሚሊየን ዝቅ እንዲል መደረጉን አመልክተዋል።
በማህበረሰብ ጥምረት አማካኝነት ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ ሀብት መሰብሰቡንና ከ200 ሺህ በላይ ቤተሰቦች እንዲደገፉ መደረጉን ጠቁመዋል።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ከመመለስ አንጻር ባለፉት ሦስት ወራት 30 ሺህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ተመላሾቹ ማህበራዊና የሥነ-ልቦናዊ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉንና በሥራ እድልና በብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
በዮናስ ጌትነት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.