Fana: At a Speed of Life!

ከ2 ሺህ በላይ መውለጃቸው ለደረሱ እናቶች ማቆያ ማዕከል ተገነባ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 2፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህብረተሰቡ የሚተዳደሩ ከ2 ሺህ በላይ መውለጃቸው ለደረሱ እናቶች ማቆያ ማዕከል መገንባቱን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት የእናቶች ጤና ባለሙያ አቶ ሸለመው ሚኔሳ፥ እናቶች በጤና ተቋም እንዳይወልዱ የሚያደርጋቸውን የመጓጓዣ እጥረትና የቦታ ርቀት ችግርን ለመፍታት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ግንዛቤ ከማስጨበጥ እና መጓጓዣ አምቡላንስ ከማዘጋጀት ባለፈ እናቶች በጤና ተቋም አቅራቢያ እንዲቆዩ የሚያስችል ማዕከል እየተዘጋጀ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የነፍሰ ጡሮች የቅድመ ወሊድ ክትትል እና በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ከአራት ዓመት በፊት ከነበረበት የ28 በመቶ ወደ 50 በመቶ ማደጉንም ጠቁመዋል።

በዚህም ባለፉት አራት አመታት በተሰራ ስራ እስከ ሁለት ሳምንት የሚደርስ የመውለጃ ጊዜ የቀራቸው እናቶች በጤና ተቋም አቅራቢያ እንዲቆዩ መደረጉን አስታውሰዋል።

የማቆያ ግንባታ ቁሳቁስ ከማቅረብ ጀምሮ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉን የገለጹት ባለሙያው፥ የሚሰሩት ማቆያዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህልና ወግ መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እናቶች በማቆያው ውስጥ በሚሆኑበት ወቅት የጤና ትምህርት እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ በመኖሪያ ቤታቸው ያለው እንክብካቤ ሳይጓደል እንደሚደረግላቸው ኢዜአ ዘግቧል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.