በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ወርቅና የውጭ ሀገራት ገንዘብ ተያዘ
አዲስ አበባ ሐምሌ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ ከ33 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ወርቅና የውጭ ሀገራት ገንዘብ መያዙን ጉሙሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ግምታዊ ዋጋቸው 33 ሚሊየን 842 ሺህ 600 ብር የሆኑ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች እና ወርቅ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር ለማስወጣት በእንቅስቃሴ ላይ እያለ በድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በቁጥጥር ስር መዋሉን የጉሙሩክ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመላሽ ተሾመ እንደገለጹት÷ 6 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ፣ 182 ሺህ 665 የአሜሪካ ዶላር፣ 68 ሺህ 905 የሳዑዲ ሪያል፣ 1 ሺህ 800 የእንግሊዝ ፓውንድ፣ 5 ሺህ 530 የካናዳ ዶላር እና 40 የባህሬን ዲናር ተይዘዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉሙሩክ ኮሚሽን፣ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት እንዲሁም በክልሉ ፖሊስ የተቀናጀ ዘመቻ መያዛቸውን ተገልጿል፡፡
ግለሰቦቹ በሕግ ጥላ ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን÷ የተያዙት ገንዘቦች ተመንዝረው ለመንግሥት ገቢ መደረጋቸውን እና ወርቁን ደግሞ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለመውሰድ ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ደመላሽ አስታውቀዋል፡፡