በአምባሰል ወረዳ 26 የሞርታርና የላውንቸር ተተኳሾችና 27 የሞርታር ቅንቡላ ማቀጣጠያ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ 03 ቀበሌ ልዩ ስሙ ሮቢት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 25 የሞርታር ተተኳሽ፣ 1 የላውንቸር ተተኳሽ እንዲሁም 27 የሞርታር ቅንቡላ ማቀጣጠያ ተገኘ፡፡
የአምባሰል ወረዳ ሚሊሻ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እሸቱ ንጉሴ÷ በዛሬው ዕለት የተገኘው የሞርታርና የላውንቸር ተተኳሽ እንዲሁም የሞርታር ቅንቡላ ማቀጣጠያ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከአካባቢው ሲሸሽ ጥሎት እንደሄደ ተናግረዋል፡፡
ተተኳሹና ማቀጣጠያው የተገኘው በህብረተሰቡ ጥቆማና ለፀጥታ ኃይሎች በተሰጠ ስምሪት መሆኑንም ገልፀዋል።
የጦር መሳሪያዎቹ ጉዳት ስለሚያስከትሉ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበው÷ በቀጣይም ሌሎች ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ የጥቆማ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡
የፀጥታ ኃይሉ የሚያደርገውን አሰሳም አጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን የወረዳው ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በአምባሰል ወረዳ በሕገ ወጥ መንገድ ተጥለው የተገኙ የሞርታር ተተኳሾች ብዛት የዛሬውን ጨምሮ 461 መድረሱም ተመላክቷል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!