በሰሜን ሸዋ ዞን ቅንብቢት ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ3 ሰዎች ሕይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቅንብቢት ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ዲቭዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ታከለ ቶሌራ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በአደጋው ሦስት ቻይናውያን ሕይወታቸው ሲያልፍ በ10 ሰዎች ላይ ከባድና 9 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል፡፡
አደጋው የተከሰተው በትናንትናው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ በዞኑ ቅንቢቢት ወረዳ ሀሙስ ገበያ ተብሎ በሚጠራው ቦታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የትራፊክ አደጋው የደረሰው÷ ከደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስና ከአዲስ አበባ ወደ ደብረብርሃን ሲጓዝ ከነበረ “ፒክአፕ” የግል ተሽከርካሪ ጋር በተፈጠረ ግጭት ነው፡፡
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ገልጸው÷ በዚህ አደጋ “ፒክአፕ” ሲያሽከረክር የነበረው አሽከርካሪ ሕይወቱ ሲያልፍ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ አሸከርካሪው ከባድ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችም ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑን ኢንስፔክተር ታከለ ቶሌራ ተናግረዋል፡፡
በአላዩ ገረመው
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!