ኢትዮጵያ በ17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት በምታስተናግደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሀገራት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበች።
ከዋናው ጉባኤ በፊት የሚካሄዱ ጉባኤዎች አካል የሆነው 11ኛው የአፍሪካ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ በአካል እና በኦንላይን ጥምረት በማላዊ ተካሂዷል።
በጉባኤው ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፥ ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት በምታስተናግደው 17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የማላዊው ጉባኤ ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ትልቅ ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ኢትዮጵያ ጉባኤውን በስኬት ለማስተናገድ ያላትን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እና ስታራቴጂው የያዛቸው የዲጂታል አካታችነት እና ዲጂታል ክህሎት ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ የተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።።
በኢትዮጵያ የሚካሄደው ጉባኤ ከኢንተርኔት አስተዳደር ጋር በተያያዘ የአፍሪካ ሀገራት ያሉባቸው ችግሮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚጠቁም እና ለፖሊሲ አውጪዎች መነሻ ሀሳብ የሚገኝበት እንዲሆን እንሰራለንም ነው ያሉት።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለአፍሪካ ሀገራት እንደ ሞዴል የሚወሰድ ነው በሚል በመድረኩ አድናቆት ተችሮታል ተብሏል።