እስካሁን በኢትዮጵያ በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተያዘ ሰው አለመኖሩ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እስካሁን በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተያዘ ሰው አለመኖሩን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ወቅታዊ የጤና ወረርሽኞችን አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በመግለጫቸው ÷በዓለም ጤና ድርጅት የጤና ስጋት ተብሎ የታወጀው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታን የመከላከል ሥራዎች ከውጭ ሀገር በሚገቡ ተጓዦች እና በስደተኞች እንዲሁም በድንበር መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ ክትትሎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
የኮቪድ 19 አሁናዊ ሁኔታን ያነሱት ዳይሬክተሩ ከሰኔ እስከ ሐምሌ ወር 2014ዓ.ም ብቻ 11 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን እና 35 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
የቫይረሱ ሥርጭትም እየጨመረ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በመግለጫው የወባ ወረርሽኝ አሁናዊ ሁኔታም የተነሳ ሲሆን ÷የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ ÷ በ 2014ዓ.ም ያለው ሥርጭት ከ 2013ዓ.ም ከነበረው ሥርጭት ጨምሯል ብለዋል።
በ2014 ዓ.ም 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል ያሉት ዶክተር ደረጀ አማራ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ እና ሲዳማ ክልሎች በሽታው በሥፋት የታየባቸው ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት በተደረገ ርብርብም 5 ነጥብ 5 ሚሊየን የመመርመርያ ኪቶችን እና 4 ነጥብ 5 ሕሙማንን ማከም የሚችል የፀረ ወባ መድሀኒት እንዲሁም 3 ሚሊየን አጎበር ተሰራጭቷል ብለዋል ዶክተር ደረጄ።
አሁን ላይም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት እየተደረገ ነው ብለዋል።
የኩፍኝ ክትባትን እና ነገ በዓለማቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የ”ሄፒታይተስ” በሽታን አስመልክቶም እንደ ሀገር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በመግለጫው ተነስተዋል።
በዙፋን ካሳሁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!