ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ከአውሮፓ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ከአውሮፓ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዶክተር አነተር ዊበር ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ገለፃ አድርገውላቸዋል።
የህወሓት የሽብር ቡድን በክልሉ እና በሌሎች አካባቢዎች ያደረሰውን ሰብዓዊ ጥሰት እና ሌሎች ጉዳዩች ያስረዱ ሲሆን÷ ቡድኑ ለሰላም ምንም ዓይነት በር የማይከፍት እና ሁልጊዜ ጦርነት እንደጎሰመ ነው ብለዋል።
የአማራ ህዝብ በሽብር ቡድኑ የጅምላ ጭፍጨፋን ጨምሮ ሌሎች ሰብዓዊ ጥቃት ሲደርስበት መቆየቱን አሁንም ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የሚገኙ ንፁሃን ዜጎች በስቃይ ላይ እንደሚገኙም ገልፀዋል።
የጦርነት አስከፊነትን ጠንቅቀን እንረዳለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ቡድኑ ወደ ስልጣን ሲመጣ በ1983ዓ.ም የፌደራል ስርዓትን ያልተከተለ በሃይል ዜጎችን በመጠቅለል ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በጣሰ መልኩ የክልል አደረጃጀቶችን ፈጥሯል ሲሉ ገልፀዋል።
በዚህም የወልቃይት ጠገዴ እና የራያ እና አካባቢው የአማራ ተወላጆች ላለፉት ጊዜያት በችግር ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በአሁኑ ሰዓት የፌደራል መንግስት የተለያዩ የሰላም አማራጮችን በማስቀደም ሃገራዊ የምክክር ኮሚሽን እና ሃገራዊ የድርድር ኮሚቴ አቋቁሞ እና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ጥረት እያደረገ እንደሚገኙ ገልፀው የአውሮፖ ህብረትም ሃገሪቱ ለምታደርገው ጥረት ድጋፍ እንዲያደረግ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እንዲሁም በአማራ ክልል ለሚያከናውነው ሁለንተናዊ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በምንይችል አዘዘው
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!