የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ከደረሰብን መከራና ፈተና ይልቅ ለተሰጠን ጸጋ በማመስገን ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት እንዳለብን የሚያሳይ ነው – ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያስተላለፉት መልዕክት ከደረሰብን መከራና ፈተና ይልቅ ለተሰጠን ጸጋ በማመስገን ለኢትዮጵያ ከፍታ መትጋት እንዳለብን የሚያሳይ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ዛሬም እንደ ትናንቱ ፈተናዎችን በድል ተሻግረን፣ እጃችንን ለምስጋና እንዘረጋለን!!” በሚል የምስጋና መልዕክት አስተላለፈዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በሚኒስትር ማእረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ እንድታሸንፍ ላደረጓት ፈጣሪና ህዝቧ ምስጋናን የሚቸር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሀገር ሆና እንዳትቀጥል በርካታ የውጭና የውስጥ ፈተናዎች ቢያጋጥሟትም በዜጎች አንድነትና ጥንካሬ እንዲሁም በፈጣሪ ሃይል መሻገሯን ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
መልዕክታቸው በዜጎች ዘንድ የአመስጋኝነት ስነልቦና እና ባህል እንዲዳብር ጥሪ የተላለፈበት መሆኑንም ዶክተር ቢቂላ አብራርተዋል።
ከአማራሪነትና ከተሸናፊነት ይልቅ አመስጋኝና ብሩህ ተስፋ ሰናቂ መሆን እንደሚገባ ጠቃሚ መልእክት የተላለፈበት ስለመሆኑም ተናግረዋል።
የበርካታ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሃብቶች ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ሀብቷን በሚመኙና ገናና ታሪኳን ማኮስመን በሚፈልጉ ሃይሎች የፈተና ውርጅብኝ ማስተናገድንም ያስታወሱበት መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ተስፋና መከራ፣ አንድነትና ልዩነት፣ ዓለም አቀፋዊ አድናቆትና ውግዘት፣ እመርታና ጉተታ መስተዋሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው መጥቀሳቸውን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በእነዚሁ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነጻነትና ግጭት ማስትናገዷን ጠቅሰው፤ በቁርጥ ቀን ልጆቿና በፈጣሪ ቸርነት ፈተናዎችን መሻገር መቻሏንም አንስተዋል።
በዚህም ለዓመታት የተጓተተውና ግንባታው ሊቋረጥ ነው ተብሎ የተነገረለትን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨት እንዲጀምር በማድረግ የኢትዮጵያ የተስፋ ጎህ መጀመሩን ገልጸዋል።
በእርዳታ እህል ልመና የምትታወቀው ሀገር በቅርቡ ስንዴ መላክ የምትችለበት ደረጃ ላይ መድረሷን አንስተው፤ ይህም ከደረሰብን ፈተና እና መከራ ይልቅ የተደረገልን መልካም ነገር ላይ ማተኮር እንዳለብን ጠቃሚ መልእክት ያስተላለፉበት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው ፈተናዎችን በድል እያለፉ ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ በምስጋና እና በትብብር በማጠናከር ጠንካራዋንና የማትንበረከከዋን ኢትዮጵያን ማስቀጠል አለብን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚነስትሩ እንዳሉትም ከዚህ ቀደም በጎ ያደረጉና ሀገራችንን ለዚህ ደረጃ ያበቁ ዜጎችን፣ መሪዎችንና ፈጣሪን ማመስገን ከሁላችንም ይጠበቃል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና ያስመዘገበው አኩሪ ድል ከተባበርን በድል አድራጊነታችን እንደምንቀጥልና መሰናክሎችን ሁሉ እንደምንሻገራቸው ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
አትሌቶቻችን በዓለም አደባባይ በፈፀሙት ጀግንነት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ከፍ እንዲልና ክብሯ እንዲወሳ አድርገዋል ብለዋል።
በዚህም መንግሥት ለአትሌቲክስ ቡድኑ የጀግና አቀባበል እንሚዲያደርግ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ታመስግን የሚል መርሃ ግብርም በነገው ዕለት እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።
መርሐ ግብሩ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ተቋማት ሠራተኞችና አመራሮች ከቀኑ 9፡00 ላይ ቀኝ እጃቸውን በግራ ደረታቸው ላይ በማሳረፍ ለአንድ ደቂቃ በፅሞና ቀና ብለው በምስጋና ልቦና የሚቆዩበት ሥነ ስርዓትም ይከናወናል።
ቀጥሎም ሁሉም ኢትየጵያውያን ለአንድ ደቂቃ በእልልታና በጭብጨባ ፈጣሪን፣ ዜጎችንና መሪዎቿን የሚያመሰግኑ ይሆናል ብለዋል።