እስራዔል በሥራ ዕድል ፈጠራ ያላትን ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ እና ክኅሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ ከእስራዔል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ወይዘሮ ሙፈሪሃት ውይይቱን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ እስራዔል በርካታ ውጤታማ የንግድ ሥራዎች ያሉባት፣ የዓለማችን ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እና ለቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎች ምቹ ምኅዳር ያላት ናት ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ እስራዔል በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አልፋ በከፍተኛ መጠን የሥራ አጥ ቁጥሯ ዝቅ እንዲል ማድረጓንም አንስተዋል፡፡
በቀጣይም ይህን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እንዲሁም በክኅሎት ልማት የግሉን ዘርፍ በባለቤትነት ያሳተፉበትን አግባብ ብሎም ለቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራዎች ምቹ ምኅዳር በመፍጠር የዓለማችን ቀዳሚ ሀገር የሆነችበትን ሚስጥር ለኢትዮጵያ ለማካፈል እስራዔል ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደሩ መናገራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም እስራዔል በሥራ ባሕል፣ በሙያ ደኅንነትና ጤንነት ላይ ያላትን ልምድ እንደምታካፍል እና በአጫጭርና በረዥም ጊዜ ሥልጠናዎች በኢትዮጵያ ያለውን የሰው ኃይል ለማብቃት እንደምትሠራ ያላትን ቁርጠኝነት ማረጋገጧን ገልጸዋል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራትም ከቀደሙት የሚጠቅሙ ምርጥ ልምዶችን ወስደው ችግሮቻቸውን መፍታትና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ወይዘሮ ሙፈሪሃት ምርጥ ልምዶች እና ተሞክሮዎች በመውሰድ ችግሮችን ለመፍታትና የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል፡፡